የኢጋድ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን አባላት በተገኙባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ሁሉ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ በታቀደለት ሰዓት መጀመሩን በመግለጫው አረጋግጧል።
በየጣቢያዎቹ በቂ የምርጫ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶች መቅረባቸውን የጠቆመው ቡድኑ፣ የምርጫ ጣቢያዎቹ አቀማመጥ ለድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ግልጽነት እና ለመራጮች እንቅስቃሴ እጅግ ምቹ እንደነበሩም አስታውቋል።
በምርጫው ዕለት በጣቢያዎች ረጃጅም ሰልፎች የነበሩ ቢሆንም፣ መራጩ ሕዝብ በከፍተኛ ትዕግሥት እና እርጋታ ድምፁን መስጠቱ በመግለጫው ተነሥቷል።
የፀጥታ ኃይሎችም በየአካባቢው የተሰጣቸውን ሕዝባዊ አደራ በመጠበቅ ለምርጫው ሂደት ሰላማዊነት ከፍተኛ እና በጎ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ተመላክቷል።
በምርጫው ሂደት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በሚገባ መወጣታቸውን ያደነቀው የኢጋድ ታዛቢ ቡድን፤ አጠቃላይ የምርጫው ሂደት ከምንም በላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለዴሞክራሲ ግንባታ ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት በግልጽ ያሳየ መሆኑን አብራርቷል።
በለሚ ታደሰ