የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ቃል 6 ሚሊዮን ችግኞች የሚተከሉበትን የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በይፋ ማስጀመሩን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።
የማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር እና የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖተ አባቶች፣ አባ ገዳዎች እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በበሻሌ ወንዝ ዳርቻ ተካሂዷል።

ከንቲባ አዳነች በመርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ ዘመን የማይሽረው ታሪክ ማስቀመጧን ገልጸዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት በመላው ኢትዮጵያውያን ርብርብ በሀገር አቀፍ ደረጃ 48 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ያስታወሱት ከንቲባዋ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 90 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸውን አብራርተዋል።
በዚህም የተነሣ የከተማዋ የአረንጓዴ ሽፋን ከነበረበት እጅግ ዝቅተኛ የ2.8 በመቶ ምጣኔ ወደ 24 በመቶ ማደግ መቻሉን አስታውቀዋል።
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ የተራቆቱ አካባቢዎች አረንጓዴ መልበሳቸውን እና የነጠፉ ወንዞች ማንሰራራት መቻላቸውን ገልጸው፣ መዲናዋም ንፁህ፣ ውብ፣ ለመኖር ምቹ እና የቱሪስት ማዕከል መሆን መቻሏን አብራርተዋል።

"የምንተክለው ተስፋን፣ ልማትን፣ ልምላሜን፣ ጥላን፣ ምግባችንን ብሎም ብልጽግናን ነው" ያሉት ከንቲባዋ፣ ተግባሩ ለዛሬ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድ የልምላሜ እና የብልጽግና ምንዳን ለማውረስ የተደረገ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።
መላው የከተማዋ ነዋሪዎች ሕፃን አዋቂ ሳይል በወንዝ ዳርቻዎች፣ በጤና፣ ትምህርት እና ሃይማኖት ተቋማት፣ በግል ሴክተሮች እና በጎዳናዎች ላይ ለምግብነት የሚውሉ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን፣ እንዲሁም የጥላ እና የውበት ዛፎችን በስፋት በመትከል ከተማዋን ውብና ለኑሮ ምቹ የማድረግ ሥራውን እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።
አያይዘውም መትከል ብቻ በቂ ባለመሆኑ፣ ኅብረተሰቡ የተተከሉ ችግኞችን በአግባቡ የመከታተል እና የመንከባከብ ኃላፊነቱን እንዲወጣ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ባሰፈሩት መልዕክት አሳስበዋል።