የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በምርት ሥራ ላይ የተሰማሩ ኢንቨስትመንቶችን፣ የኃይልና የውሃ መሠረተ ልማቶችን የጎበኙ ሲሆን፤ በነፃ ንግድ ቀጠናው በሚከናወኑ ሥራዎች ዙሪያም ከባለሀብቶችና ከባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ውይይት አካሂደዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት የክልሉ ዋነኛ ትኩረት አዳዲስ ኢንቨስተሮችን መሳብ ብቻ ሳይሆን አምራችነትን፣ ተወዳዳሪነትንና ብልጽግናን መፍጠር የሚችል ጠንካራ የኢኮኖሚ ሥርዓት መገንባት ሲሆን ለዚህ ዓላማ ስኬት ደግሞ የልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ሚና ከፍተኛ ነው።
የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ችግር የሀብት እጥረት ሳይሆን ያለውን ሀብት ወደ ተጨማሪ እሴት አለመለወጥ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የተሟላ የአምራችነት ሥርዓት ለመገንባት እርስ በእርስ በተሳሰሩ አራት ዋና ዋና ምሰሶዎች ማለትም ታላላቅ የኢንዱስትሪ ማዕከላትንና ፓርኮችን በማስፋፋት፣ የከተሞችና የዞኖችን የኢንቨስትመንት ሥነ-ምህዳር በማሻሻል፣ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች በሀገር ውስጥ በስፋት እንዲመረቱ በማድረግ እንዲሁም ወጣቶችን በክህሎት በማስታጠቅ በሥራ ፈጠራ ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ በማስቻል ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል።
አስተማማኝና ዘላቂ አምራችነት ሊቀጥል የሚችለው በጠንካራ መሠረተ ልማት ላይ ሲገነባ መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለዚህም ሲባል የውኃ፣ የኃይልና ሌሎች የኢንቨስትመንት ደጋፊ የሆኑ መሠረተ ልማቶች የአምራችነት ሥርዓቱ አካል ተደርገው እየተሟሉ መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህ መሠረተ ልማት ጎን ለጎን የገዳ ነፃ ንግድ ቀጠና ምርትን ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር የማገናኘት፣ ተወዳዳሪነትን የማጠናከርና የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት ስትራቴጂካዊ በር ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝም ተብራርቷል።
በክልሉ እየተተገበረ የሚገኘውን የሪፎርም መርሃ ግብር ያነሱት አቶ ሽመልስ፤ በ"ሓሮሜ" መርሃ ግብር ገጠርን ወደ አምራችነት ማዕከል ለመለወጥ እየተሠራ ባለበት ሁኔታ፣ በገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጠና ደግሞ ያንን የገጠር አምራችነት ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪና ተጨማሪ እሴት በማሸጋገር ወደ ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ኃይል እየተቀየረ ይገኛል ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጠና ከሀሳብ ወደ ተጨባጭ ተግባር እንዲቀየር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት የዞኑ (ZDAG) ቦርድ ሰብሳቢና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።