በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በተቋማዊ መልኩ መመራቱ ይበልጥ ውጤታማ እንዳደረገው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገልጸዋል።
አፈ ጉባኤው ይህንን የተናገሩት 8ኛውን ዙር የአዲስ አበባ ከተማ የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ባስጀመሩበት ወቅት ነው።
የዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ከአንድ ትልቅ ሀገራዊ ሁነት ማግስት የሚካሄድ መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ጠቅሰዋል፡፡
አፈ ጉባኤው የፖለቲካ ፓርቲዎች በእንዲህ ዓይነት ሀገራዊ ሥራ ላይ እያደረጉት ያለው ንቁ ተሳትፎ ለጋራ አገር በጋራ የመሥራት ባህል የታየበት ድንቅ ተግባር መሆኑን አንስተዋል።

የሁሉም መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ከተማ በብዙ መልኩ እየተቀየረች የምትገኝ ሲሆን፣ ይህም ሊሆን የቻለው የለውጥ አመራሩ ራስን ለሕዝብ የመስጠት ጥበብን በተግባር በማሳየቱ መሆኑን አቶ አገኘሁ ተናግረዋል።

በከተማዋ በብርቱ ጥረት በተሠሩ ሥራዎችም አዲስ አበባን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ከተማ ማድረግ እየተቻለ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በነቂስ ወጥቶ በራስ ተነሳሽነት ሊተገብረው እንደሚገባ አፈ ጉባኤ አገኘሁ አሳስበዋል።
በይመር አደም