Search

የባሕር በር ለኢትዮጵያ፡ የተፈጥሮ ሕግ ፍትህ

ቅዳሜ ሰኔ 13, 2018 54

ባሕር ለኢትዮጵያ የንግድ ሸቀጥ መተላለፊያ ብቻ አይደለም፤ ከምንም በላይ የታሪክ፣ የባህል እና የስነ-ልቦና ትስስር መልሶ ማገናኛ ታላቅ ብሄራዊ ድልድይ ነው።

የቀይ ባሕር ሞገዶችና የሕንድ ውቅያኖስ ወጀቦች የኢትዮጵያን ታሪክ የፃፉት በውሃ ላይ ብቻ ሳይሆን በህዝቦቿ ስነ-ልቦና እና ማህበራዊ የደም ስር ውስጥ ጭምር ነበር።

አብዛኛውን ጊዜ ስለ ባሕር በር የሚነሱ ትረካዎች በንግድ ሚዛን፣ በኮንቴይነር ፍሰትና በጂኦ-ፖለቲካዊ የበላይነት ስሌት ላይ ያተኩራሉ። ነገር ግን የኢትዮጵያ እና የባሕር ትስስር ከኢኮኖሚ ቀመር በላይ የጠለቀ፣ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ የመተንፈስና የመዘርጋት ፍላጎት መገለጫ ነው።

ባህሩ ለኢትዮጵያ መለያያ ግንብ ሳይሆን ታላላቅ ስልጣኔዎችን ያቆራኘ ሰማያዊ ድልድይ፣ የአክሱምና የአዱሊስ ህያው ምስክር እንዲሁም የዘይላ፣ የምጽዋ፣ የታጁራና የበረበራ ወደቦች የሀገራችን የእትንፋስ መስመሮች ነበሩ።

ከሶስት አሰርት ዓመታት በፊት የተፈጠረው ታሪካዊ ስብራት ግን ይህንን ሰማያዊ ድልድይ ወደ ሰው ሰራሽ ግንብ ቀየረው።

No photo description available.

ኢትዮጵያ ያለ አግባብ የባህር በር አልባ እንድትሆን መደረጓ ተራ የድንበር ለውጥ ሳይሆን የሺህ ዓመታት የታሪክ፣ የባህል እና የደም ትስስርን በአንድ ጀምበር የበጠሰ ማህበራዊ ድንጋጤ ነበር።

በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ካሉ የባህር በር አልባ ሀገራት በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀሰውና እጅግ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት ሀገር፣ መላው የገቢና ወጪ ንግዷ፣ የደህንነት ስጋቷ እና የነገ ተስፋዋ በአንድ ጠባብ አቅጣጫ ብቻ ታንቆ እንዲኖር መፍቀድ የትኛውንም የሞራል እና የፍትህ ሚዛን የሚደፋ አይደለም።

በመሆኑም ዛሬ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት የሌሎችን ሉዓላዊነት የመጋፋት ፍላጎት ሳይሆን የተሰበረዉን ድልድይ የመጠገን ፍትሃዊ ጥያቄ ነው።

“የውሃ ጥማት በህልም አይረካም” እንዲሉ ይህ ጥያቄ በጊዜያዊ ምኞት የሚተው ሳይሆን የህልውና እና የብሔራዊ ኩራት ጉዳይ ነው።

አሁን እየተሄደበት ያለው የዲፕሎማሲ መንገድ ያለፈውን ዘመን የወራሪዎችን የጉልበት አካሄድ በሰለጠነና በዘመናዊ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ የሚተካ ታሪካዊ እርምጃ ነው።

የቀድሞዎቹ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎችና ጀግኖች አባቶች በደምና በአጥንት ጠብቀው ያቆዩትን አደራ ማደስ፣ ለቀጣዩ ትውልድ በራሷ የምትተማመንና የተሟላ ሉዓላዊነት ያላት ሀገር የማውረስ ጉዳይ ነው።

የኢትዮጵያ የነገው ብሩህ ተስፋ ከተፈጥሯዊ የባሕር በሯ ውጭ ሙሉ ሊሆን እንደማይችል ሁሉ ይህንን ፍትሃዊ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ መመለስም የቀጣናውን ዘላቂ ሰላምና አብሮነት የሚያረጋግጥ የታሪክ እውነት ነው።

በመሆኑም የባሕር በር ጥያቄው ወደ ቀደመው የተፈጥሮ ህግ የመመለስ የፍትህ ጉዞ ነው።