Search

የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታዎች ካላቸው በሕጋዊ መንገድ ብቻ መፍታት ይኖርባቸዋል - የኢጋድ ታዛቢ ቡድን

ረቡዕ ግንቦት 26, 2018 116

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) የምርጫ ታዛቢ ቡድን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫው ጋር ተያይዞ ለሚነሡ ማናቸውም ቅሬታዎች ሕጋዊ መንገዶችን ብቻ መከተል እንዳለባቸው አሳስቧል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ኢትዮጵያውያን በውስጥ ጉዳዮቻቸው ራሳቸው እንዲወስኑ ዕድል እንዲሰጥም ቡድኑ ጥሪ አቅርቧል።

ቡድኑ አክሎም በሂደቱ የሴቶች ተሳትፎ መሻሻል እንዳለበት ያመላከተ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጀመረው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማጠናከር እንዳለበት አስተያየቱን ሰጥቷል።

የፀጥታ አካላት ምርጫውን ሰላማዊ ለማድረግ የጀመሩትን ገለልተኛ የፀጥታ ጥበቃ ሥራ አጠናክረው ማስቀጠል እንዳለባቸውም ነው ታዛቢ ቡድኑ ያስገነዘበው።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በበኩላቸው በምርጫ ሂደቱ ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ እና ለሕዝቡ የሚሰጡትን የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ በማጠናከር በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ ጠቁሟል።

ከምርጫው በኋላም ቢሆን በኢትዮጵያ የንግግር እና የውይይት ባህል እንዲዳብር የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብሏል።

መንግሥት ለዴሞክራሲ ግንባታ እያደረገ ያለውን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል እና ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖረው ጠንካራ ሥራ መሥራት እንዳለበት መግለጫው ተመላክቷል።

ለዚህም መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበት አስምሮበታል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያውያን ለገጠሟቸው ችግሮች ራሳቸው መፍትሔ እንዲሰጡ እና የውስጥ ጉዳያቸውን በራሳቸው እንዲፈቱ ዕድል ሊሰጥ እንደሚገባ የኢጋድ ምርጫ ታዛቢ ቡድን ጥሪውን አቅርቧል።

 

በለሚ ታደሰ