Search

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 23ኛ መደበኛ ስብሰባ ነገ ይካሄዳል

ረቡዕ ግንቦት 26, 2018 106

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5 ዓመት የሥራ ዘመኑ 23 መደበኛ ስብሰባውን ነገ ግንቦት 27 ቀን 2018 . ያካሂዳል።

ምክር ቤቱ በነገው ስብሰባው በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ልማት ባንክ እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር መካከል የተደረጉ የብድር ስምምነቶችን ለማጽደቅ የወጡ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በኢፌዴሪ መንግሥት እና በሴራሊዮን ሪፐብሊክ መንግሥት፤ በኢፌዴሪ መንግሥት እና በአንጎላ ሪፐብሊክ መንግሥት፤ በኢፌዴሪ መንግሥት እና በባንግላዲሽ ሕዝባዊ ሪፐብሊክ መንግሥት፤ እንዲሁም በኢፌዴሪ መንግሥት እና በኢስዋቲኒ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት መካከል የተፈረመውን የሁለትዮሽ የአየር አገልግሎት ስምምነት ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀርበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁን የሚያጸድቅ ይሆናል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ በኢፌዴሪ መንግሥት እና በሩሲያ ፌዴሬሽን መካከል የጋራ የባዮሎጂ ምርምር ማዕከል ለማቋቋም የተፈረመውን ስምምነት ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀርበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁን እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።

በተያያዘም በኢፌዴሪ መንግሥት እና በቬትናም ሶሻሊስት ሪፐብሊክ መንግሥት መካከል የዲፕሎማቲክ ወይም ኦፊሴላዊ የአገልግሎት ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን ለማስቀረት የተፈረመ ስምምነት ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀርበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁን ያጸድቃል።

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የፌዴራል ታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን፣ የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ረቂቅ አዋጅን፣ የምግብ ሥርዓትና ሥርዓተ ምግብ ረቂቅ አዋጅን፣ የኢትዮጵያ የካርበን ገበያ ረቂቅ አዋጅን እና የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች የሚመራ መሆኑን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።