Search

የ5ቱ ዓመታት ገፆች፦ ዲጂታል ኢትዮጵያ ከህልም ወደ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት

ዓርብ ሰኔ 05, 2018 90

ዓለማችን በቴክኖሎጂ ማዕበል በፍጥነት እየገሰገሰች ነው። የሰው ልጅ የእውቀት እና የፈጠራ አድማስ በየሰከንዱ ይሰፋል። ይህን ተለዋዋጭ የዲጂታል ዘመን በንቃት መረዳት የግድ ይላል።

ከስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ አንስቶ ወደ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዋዜማ ስንሸጋገር የተፃፉት የአምስቱ ዓመታት ገፆች ደግሞ፣ ኢትዮጵያ ይህንን ዓለም አቀፍ ሁኔታ ቀድማ መገንዘቧን ያመለክታል። 

በመሆኑም የራሷን አዲስ የዲጂታል አብዮት ትርክት በደማቁ እየጻፈች ትገኛለች። ዘመኑ ሰው ሠራሽ አስተውሎት እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የነገሡበት ነው።

ኢትዮጵያ ከኋላ ተከታይነት ወደ ግንባር ቀደም መሪነት የሚያሸጋግራትን ትክክለኛ መንገድ መርጣለች። የሀገራችን የኢኮኖሚ ዕጣ ፈንታ ከልማዳዊ አሠራር ወደ ዕውቀት መር በመቀየር ላይ ይገኛል።

የዚህ ታሪካዊ ሽግግር ደማቅ ማሳያ የአምስት ሚሊዮን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ ነው። ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ከታቀደለት ጊዜ ቀድሞ ተሳክቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) እንዳበሰሩት፣ በሦስት ዓመታት የታቀደው ግብ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ እውን ሆኗል።

ከግማሽ አስርት ሚሊዮን በላይ ዜጎች በፕሮግራሙ ተመዝግበዋል።

ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ሥልጠናቸውን በስኬት አጠናቀዋል። ወጣቶቹ በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ዴቨሎፕመንት፣ በዳታ ሳይንስ እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዓለም አቀፍ ዕውቀትን ታጥቀዋል። ይህ ታላቅ ስኬት የሕዝባችንን ቁርጠኝነት እና ወሰን የሌለው አቅም በተግባር ያረጋግጣል።

የዲጂታል ክህሎት በአንድ ሀገር የኢኮኖሚ መዋቅር ላይ ትልቅ ፋይዳ አለው። እንደ ሕንድ፣ ኢስቶኒያ እና ደቡብ ኮሪያ ያሉ ሀገራት በቴክኖሎጂ የደረሱበትን ከፍታ መመልከት በቂ ነው።

ሕንድ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿን ከድህነት አውጥታለች። ኢስቶኒያ እጅግ ዘመናዊ ዲጂታል ማኅበረሰብ ገንብታለች።

ደቡብ ኮሪያ ደግሞ ቴክኖሎጂን የኢኮኖሚዋ የጀርባ አጥንት አድርጋለች። የኢትዮጵያ ወጣቶችም የዚህ ዓለም አቀፍ የሥራ ገበያ ተወዳዳሪ እየሆኑ ነው። ከሠልጣኞቹ አስር በመቶዎቹ እንኳን ወደ ሥራ ቢገቡ፣ በየዓመቱ እስከ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ወደ ሀገር ውስጥ ይገባል። ይህም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ራዕይ ዋነኛ ምሰሶ ነው።

ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) ቴሌብር እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት የዳበሩ መተግበሪያዎች የዚህ ራዕይ ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው። ሀገራችን ከዘመኑ የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር እኩል እየተራመደች መሆኗን በተግባር እያሳየች ነው። የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዳረጋገጠው፣ ይህ የሰለጠነ የሰው ኃይል የሀገሪቱ የዲጂታል ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር ነው።

ይህ ደማቅ ታሪካዊ ምዕራፍ የጉዟችን ማብቂያ አይደለም። ይልቁንም ብሔራዊ ራዕያችንን ይበልጥ የምናፋጥንበት ጽኑ መነሻ ነው። እስከ ነሐሴ ሁለት ሺህ አስራ ስምንት ዓመተ ምህረት ድረስ የሠልጣኞችን ቁጥር ሰባት ሚሊዮን ለማድረስ አዲስ ግብ ተሰንቋል። መጭው ጊዜ በተለይ ለወጣት ተማሪዎቻችን ሰፊ ዕድል ይዞ መጥቷል።

ወጣቶች ጊዜያቸውን በዋዛ ማሳለፍ የለባቸውም። ይህንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያለው ነፃ ሥልጠና በመውሰድ የነገ የዲጂታል መሪዎች መሆን ይጠበቅባቸዋል።

የኢትዮጵያ የዲጂታል አብዮት ከወረቀት ወደ ተግባር፣ ከተስፋ ወደ ተጨባጭ እውነት ተሸጋግሯል። መንገዱ በርቷል፤ አቅጣጫውም ትክክል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት "የምትገነቡት ነገ የሚጀምረው ዛሬ ነው!" ዛሬ የሚዘራው የዕውቀት እና የክህሎት ዘር፣ የነገዋን የበለጸገች እና ታላቅ ኢትዮጵያ ጽኑ መሠረት ይገነባል።