የጉምሩክ ኮሚሽን ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ባደረገው ተከታታይ የክትትል ሥራ፣ በድምሩ 989 ነጥብ 99 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች መያዙን አስታወቀ።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሕገወጥ ዕቃዎች መካከል 969 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የገቢ እንዲሁም 20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የወጪ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መሆናቸው ተገልጿል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት ዕቃዎች መካከል አዳዲስና ልባሽ ጨርቆች፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የግንባታ ዕቃዎች፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫ እና የመዋቢያ ዕቃዎች ይገኙበታል።

በተጨማሪም መድኃኒቶች፣ አደንዛዥ ዕጾች፣ ማዕድናት፣ የቁም እንስሳት፣ ቡና፣ ጥራጥሬ፣ ጫት እና የውጭ ሀገር ገንዘቦች በቁጥጥር ስር ከዋሉት ዕቃዎች መካከል ይገኙበታል።
በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ የገቢና የወጪ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ የአዋሽ፣ የጅግጅጋ እና የሞያሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ቀዳሚውን ስፍራ ይዘዋል።
በዚህም መሠረት አዋሽ 675 ሚሊዮን ብር፣ ጅግጅጋ 102 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ሞያሌ 78 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸውን የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዝ ችለዋል።
እነዚህ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር ሊውሉ የቻሉት በጉምሩክ ኮሚሽን ሠራተኞች፣ በፌደራልና በክልል ፖሊስ አባላት እንዲሁም በኅብረተሰቡ የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በጥቆማና በበረራ በተደረገ ክትትል ነው።
የኮሚሽኑ መረጃ እንደሚያመላክተው ሕገወጥ ዕቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 16 ተጠርጣሪዎችና 21 ተሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የኮንትሮባንድና የሕገወጥ ንግድን በዘላቂነት ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመከላከል የኮሚሽኑ እንቅስቃሴ ብቻ በቂ አይደለም ያለው ኮሚሽኑ መላው ኅብረተሰብ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪውን አቅርቧል።