ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ አስደናቂ የዲጂታል አብዮት እያካሄደች ነው። ይህ ጉዞ ከወረቀት ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደረገ ታሪካዊ ሽግግር ነው። የዚህ አንጸባራቂ ስኬት ዋነኛ ሞተር ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የላቀ እና ፈር ቀዳጅ አመራር ነው።
የሰው ልጅ የዕለት ተዕለት ሕይወት በዲጂታል ሥርዓት እየተመራ ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘረጉት ራዕይ ኢትዮጵያን አፍሪካዊ የቴክኖሎጂ ተምሳሌት አድርጓታል። የኢትዮጵያ ሕዝብም የዚህ ፈጣን ለውጥ ቀጥተኛ ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል።
የኢትዮጵያ የዲጂታል ጥረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ አድናቆትን እያተረፈ ነው። በቅርቡ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ላይ ታላቅ ታሪካዊ ሹመት ተሰጥቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኅብረቱ የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ ሆነው በሙሉ ድምጽ ተመርጠዋል።
ይህ ልዩ ሹመት የተሰጠው እሳቸው ለዘርፉ ላበረከቱት ጉልህ እና ተጨባጭ ምስክር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቴክኖሎጂን ለአፍሪካ ሉዓላዊነት እና አሳታፊ ዕድገት ቁልፍ መሣሪያ አድርገውታል። የቴክኖሎጂ ነፃነትን እውን ለማድረግ ከፍተኛ እና የማያቋርጥ ቅስቀሳ አድርገዋል።

የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት በሀገር ደረጃ ተቋቁሟል። ብሔራዊ ስትራቴጂም በግልጽ እና በጥራት ተነድፏል። አልፎ ተርፎም ራሱን የቻለ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም ዝግጅት ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ ዲጂታል ጤና ጉዞ መሬት የነካ እና እውነተኛ ነው። ሀገሪቱ ጤናን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ አዳዲስ መተግበሪያዎችን አስተዋውቃለች። የመረጃ አያያዝ ወደ ዘመናዊ ሥርዓት ተቀይሯል። የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱም እጅግ ፈጣን እና ቀልጣፋ ሆኗል። ከነዚህም ውስጥ አንደኛው ስኬት የዲስትሪክት ጤና መረጃ ሶፍትዌር ትግበራ ነው።
የዲስትሪክት ጤና መረጃ ሶፍትዌር በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ የጤና ተቋማትን በአንድ ማዕከላዊ ቋት አገናኝቷል። የበሽታዎችን ሥርጭት በቅጽበት ለመከታተል አስችሏል። መድኃኒቶችን በትክክለኛ ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ ለማከፋፈል አግዟል። የአፍሪካ በሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል ይህንን የኢትዮጵያ አሠራር በምሳሌነት እና በአርአያነት ይጠቅሰዋል።
የቴሌ-ጤና አገልግሎት መስፋፋት ሌላው ትልቅ ዕርምጃ ነው። የጂኦግራፊያዊ ርቀትን በቀላሉ ማጥበብ ተችሏል። ቪዲዮ እና ዲጂታል ማማከር በስፋት ሥራ ላይ ውለዋል። በገጠር የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ከሪፈራል ሆስፒታል ከፍተኛ ሐኪሞች ጋር በቀጥታ ተገናኝተዋል። ታካሚዎች ለሕክምና ረጅም መንገድ መጓዝ ቀርቶላቸዋል።
የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የኢትዮጵያ ትልቅ መለያ ነው። አሁን ደግሞ ይህ ግዙፍ መዋቅር በቴክኖሎጂ በሚገባ ታግዟል። ባለሙያዎች በዲጂታል ታብሌቶች እና በሞባይል መተግበሪያዎች የዕለት ተዕለት ሥራቸውን እየሠሩ ነው። የነፍሰ ጡሮች፣ የሕፃናት እና የክትባት መረጃ በቀጥታ ወደ ማዕከላዊ ቋት ይላካል። የወረቀት ንክኪ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል። የመረጃ ጥራት እና ታማኝነት ግን እጅግ አድጓል።

በትላልቅ ሆስፒታሎችም የኤሌክትሮኒክስ የሕክምና መዝገብ ዘመናዊ ሥርዓት ተዘርግቷል። የታካሚዎች የሕክምና ታሪክ በፍጹም አይጠፋም። ከአንድ የሕክምና ክፍል ወደ ሌላው በሰከንዶች ውስጥ በቀላሉ ይተላለፋል። ታካሚው ፈጣን እና የተሳለጠ አገልግሎት ያገኛል።
የኢትዮጵያ የዲጂታል ጤና ፍኖተ-ካርታ ለአፍሪካ ኅብረት ትልቅ ማጣቀሻ ሆኗል። ውስን ሀብት ይዞ ሰፊ ማኅበረሰብን በቴክኖሎጂ መድረስ እንደሚቻል ሀገራችን በተግባር አሳይታለች። ይህ ትልቅ ስኬት የኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ ዲፕሎማሲ በአህጉሪቱ ከፍ አድርጎታል።
የጤና አገልግሎት ጥራትም በሚታይ ሁኔታ ተሻሽሏል። የጤና ሚኒስቴር ለነገዋ ኢትዮጵያ ትልቅ ግብ ሰንቋል። በአውሮፓውያኑ ሁለት ሺህ ሠላሳ ዓመተ ምህረት የጤናው ዘርፍ ሙሉ በሙሉ ወረቀት አልባ ይሆናል። የኢትዮጵያ የዲጂታል ጤና ጉዞ ለአፍሪካ አህጉር ብሩህ ተስፋ እና ትልቅ ትምህርት ነው።