የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በመተባበር "ውጤታማ ተግባቦት ለጠንካራ የጤና ሥርዓት ግንባታ" በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ መክፈቻ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ እንደገለጹት፣ በዘርፉ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችንና የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በተሳካ ሁኔታ ወደ መሬት ለማውረድ እንዲሁም ጤናው የተጠበቀ አምራች ዜጋን ለመፍጠር ውጤታማ የጤና ተግባቦት ወሳኝና የማይተካ ሚና አለው።
የጤናው ዘርፍ ሰፊና ውስብስብ ባህሪ ያለው በመሆኑ፣ አገልግሎት ፈላጊዎች ከጤና ባለሙያዎች ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት አጥጋቢ ምላሽና ተገቢውን መረጃ ማግኘት እንዲችሉ የጤና ተግባቦትን ማጠናከር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ በበኩላቸው፣ የጤና ባለሙያዎች በዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወትና ደህንነት ውስጥ ልዩ ቦታ ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የዘርፉን የተግባቦት አቅም ይበልጥ ማጎልበት በጤናው ዘርፍ ላይ አልፎ አልፎ ለሚስተዋሉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመፈለግና በአገልግሎት ሰጪውና ተጠቃሚው መካከል ጠንካራ መተማመንን ለመፍጠር እንደሚያስችል አስረድተዋል።
በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ የጤናው ዘርፍ ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን፣ በዘርፉ ስትራቴጂካዊ ተግባቦት ዙሪያ ሰፊ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።