በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ሊያስቆም ይችላል የተባለ አዲስ የዲፕሎማሲ ሐሳብ ከወደ ኪዬቭ ተሰምቷል።
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ የፊት ለፊት ውይይት ለማድረግ ለሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቀን እንዲቆርጡ ጠይቀዋል።
ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ለሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በላኩት ደብዳቤ፤ "ቀን አስቀምጥ እና ፊት ለፊት እንገናኝ" ያሉ ሲሆን፣ በገለልተኛ ሀገር ውስጥ ቀጥታ የፊት ለፊት ውይይት ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
በተጨማሪም በውይይቱ ላይ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራት እንዲገኙ እንደሚፈልጉ በደብዳቤያቸው ጠቅሰዋል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት የላኩት ደብዳቤ እንደደረሳቸው ያረጋገጡ ሲሆን፣ "ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ፑቲንን ማግኘት ከፈለጉ ወደ ሞስኮ ሊመጡ ይችላሉ" ብለዋል።
በዚህ ሰዓት የዓለም ትኩረት ያረፈው በአንድ ጥያቄ ላይ ነው፤ ፕሬዚዳንት ፑቲን የዩክሬኑ አቻቸው ያቀረቡላቸውን ጥሪ ይቀበሉ ይሆን? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል።
በቢታኒያ ሲሳይ