ኢትዮጵያ ድንበሮቿን ከጥበቃና ከማካለል ባለፈ የልማት፣ የጋራ ብልጽግና እና የሰላም መገናኛ ኮሪደር ለማድረግ የሚያስችላትን የፖሊሲ ለውጥ ማድረጓን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢትዮጵያን የድንበር አስተዳደር ማጠናከር በሚል በተካሄደው ጥናት ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ ሀገራዊ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃፋር በድሩ በኮንፈረንሱ መክፈቻ ኢትዮጵያ ለዓመታት ስትከተለው የነበረውንና ድንበሮችን እንደ "ፀጥታ ስጋት" ብቻ የመመልከት አካሄድ በመቀየር፣ አዲስ አህጉራዊ ዕይታን ያካተተ ፍኖተ-ካርታ ማፅደቋን ገልጸዋል።
ይህ አዲሱ አቅጣጫ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ በመስጠት ለድንበር አካባቢዎች ልማት ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑንም አክለዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ከዚህ ቀደም የድንበር አካባቢዎች ለመደበኛ የሰዎችና የሸቀጦች እንቅስቃሴ እጅግ ጥብቅ፣ ለሕገ-ወጥ ኮንትሮባንድና ለጦር መሣሪያ ዝውውር ግን ክፍት ሆነው ቆይተዋል።
አዲሱ ፍኖተ-ካርታ ይህንን የተዛባ አሰራር በመቀየር እንደ ፖሊስ፣ ጉምሩክ፣ ኢሚግሬሽን እና የክልል መስተዳድሮች ያሉ ተቋማት በቅንጅት እንዲሰሩ የሚያስገድድ ነው።
ይህ የፖሊሲ ለውጥ የኢትዮጵያ ደህንነትና ብልጽግና ከጎረቤቶቿ መረጋጋት ጋር የተቆራኘ ነው ከሚል ፅኑ እምነት የመነጨ ሲሆን፤ ዋነኛ ግቡም ሕጋዊው የንግድ መስመር ሕገ-ወጡን የኮንትሮባንድ መስመር አሸንፎ እንዲወጣ ማድረግ ነው።
የዚህ አዲስ ስትራቴጂ ሌላኛው ስኬት በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦችን፣ በተለይም በድንበር ተሻጋሪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶችንና ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር መዘርጋቱ ነው።
ይህ የኢትዮጵያ የፖሊሲ ሽግግር ከአፍሪካ ሕብረት የድንበር ፕሮግራም እና ከኒያሚ ኮንቬንሽን መርሆዎች ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣጣም ነው። ይህም ድንበሮችን ከሉዓላዊነት ምልክትነት ባለፈ በጋራ የሚተዳደሩ የልማት ቀጣናዎች የማድረግ አህጉራዊ እንቅስቃሴ አካል መሆኑ ተገልጿል።
ከጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት እና ከሌሎች አጋሮች ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ይህ ፍኖተ-ካርታ፤ ኢትዮጵያን ከጎረቤቶቿ ጋር በምስራቅ አፍሪካ በይነ-መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) እና በአፍሪካ ህብረት በኩል ይበልጥ በማስተሳሰር እያንዳንዱን የድንበር መስመር የሰላምና የጋራ ብልጽግና ኮሪደር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።