Search

60 ዓመታትን ለኢትዮጵያ የዱር ሕይወት

ዓርብ ሰኔ 05, 2018 48

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን 60 ዓመት የምስረታ በዓል "60 ዓመታትን ለኢትዮጵያ የዱር ሕይወት" በሚል መሪ ቃል እያከበረ ይገኛል።

የዚሁ አካል የሆነው፣ የዘርፉ ምሁራን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተሳተፉበት የዱር እንስሳት ምርምር ሴሚናር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ሴሚናሩ በዱር እንስሳትና በብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ዙሪያ የሚካሄዱ ሳይንሳዊ ጥናቶችን ከፖሊሲ እና ከተግባራዊ ጥበቃ ሥራዎች ጋር በማስተሳሰር የዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ ያለመ ነው።

የዱር እንስሳት ጥበቃን በማጠናከር ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ በብዝሃ ሕይወት ሀብት የታደለች ናት ያሉት የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታው እንደገና አበበ (/) ለዱር እንስሳት ጥበቃ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ይህም የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት እና የመስህብ መዳረሻዎችን በማሳደግ ረገድ የዱር እንስሳት ያላቸው አበርክቶ የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የፈጠራና የምርምር ውጤቶችን ይበልጥ በመጠቀም የዘርፉን አቅም ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ በዘርፉ የተደረጉ የጥናትና ምርምር ስራዎች በእውቀትና በመረጃ የተደራጀ አሰራር እንዲዘረጋ አድርጓል ብለዋል። ይህም የኢትዮጵያን የዱር እንስሳት ሀብት ለማወቅና ለመለየት እያስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከሴሚናሩ የሚገኙ ግኝቶች የዱር እንስሳትና የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ፖሊሲዎችን፣ የአስተዳደር ሥርዓቶችን እና የወደፊት የምርምር አቅጣጫዎችን ለማጠናከር አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ይጠበቃል።