Search

5ቱ ዓመታት ገፆች፦ የኢትዮጵያ ዲጂታል ክፍያ ሥርዓት እመርታ እና የኢኮኖሚው አዲስ ምዕራፍ

ዓርብ ሰኔ 05, 2018 78

ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገራችን የተከናወኑ መጠነ ሰፊ የዲጂታል መሠረተ ልማት ግንባታዎችና የፖሊሲ ማሻሻያዎች በኢትዮጵያ የክፍያ ሥርዓት ላይ ታላቅ አብዮት ፈጥረዋል።

"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" እና "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂዎች ይፋ ከሆኑ ወዲህ፣ በኢትዮጵያ ከባህላዊው የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ወደ ዘመናዊው የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ያደረገችው ሽግግር አስገራሚ ዕድገት አስመዝግቧል።

 ቀደም ሲል በኦፕሬተር የሚመራ የሞባይል ገንዘብ ሥርዓት ባለመኖሩ የጥሬ ገንዘብ ጥገኝነት መላቀቅ ተስኖ የነበረ ቢሆንም፣ የፖሊሲ ማሻሻያ ተደርጎ የኢትዮ ቴሌኮም "ቴሌብር" ወደ ሥራ መግባቱ ሁኔታዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀይሮታል።

ቴሌብር በሦስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ45 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎችን ማፍራቱ የሀገራችንን የዲጂታል አቅም ለዓለም ያሳየ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የሞባይል ዋሌት አካውንቶች ቁጥር 161 ሚሊዮን በላይ ደርሷል።

ይህም ከአጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር በላይ መሆኑ የአገልግሎቱን ተደራሽነት የሚያሳይ ሲሆን፣ በፕላትፎርሙ የሚከናወነው የገንዘብ ዝውውርም ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) 82 በመቶ ደርሷል።

ይህ የዲጂታል ክፍያ አብዮት ለሀገራዊ ኢኮኖሚው በርካታ ጥቅሞችን እያስገኘ ይገኛል።

የመጀመሪያው የፋይናንስ አካታችነት ሲሆን፣ የባንክ አገልግሎት ባልደረሰባቸው ገጠራማ አካባቢዎች ዜጎች በስልካቸው ብቻ ገንዘብ መቆጠብ፣ መላክ እና መቀበል በመቻላቸው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ወደ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው እንዲገቡ አድርጓል።

በሌላ በኩል፣ መንግሥት እንደ ነዳጅ ግብይት፣ የትራፊክ ቅጣት፣ የግብር ክፍያ እና የውኃና መብራት አገልግሎቶችን በዲጂታል መንገድ በማድረጉ ብክነትን በመቀነስ ገቢው በቀጥታ ወደ ካዝናው እንዲገባ አስችሏል፤ ለምሳሌ የነዳጅ ግብይት በዲጂታል ብቻ መሆኑ ሕገ-ወጥ ዝውውርን በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።

በተጨማሪም ብሔራዊ ባንክ ለገንዘብ ሕትመትና ጥገና የሚያወጣውን በቢሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ ለማዳን የተቻለ ሲሆን፣ የገንዘብ ምንጭና መድረሻው ስለሚታወቅ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከልና የጥቁር ገበያን ለመቆጣጠር የተሻለ አቅም ተፈጥሯል።

ባጠቃላይ ይህ ዕድገት ወደ ዘመናዊ ኢኮኖሚ ለምናደርገው ጉዞ ትልቅ ሞተር እየሆነ ሲሆን፣ ዘርፉ በፖሊሲ መደገፉን መቀጠሉ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑት የዲጂታል ምጣኔ ሀብት ተጠቃሚ ሀገራት ተርታ እንደሚያሰልፋት ይጠበቃል።