መዲናችን አዲስ አበባ ዕድሜ ጠገብና ታሪካዊ ከተማ ብትሆንም፣ ስምና ክብሯን የሚመጥን የውስጥ መሠረተ ልማት ዕድሳት ሳይደረግላት በመቆየቱ ምክንያት መንደሮቿና መንገዶቿ ለብዙ ዓመታት ለዓይን የማይማርኩና ምቾት የማይሰጡ ሆነው ቆይተዋል።

ይሁን እንጂ፣ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ በተከናወኑ ስኬታማና የተቀናጁ የልማት ሥራዎች ከተማዋ አሮጌ ገፅታዋን በፍጥነት በመለወጥ ላይ ትገኛለች።

አሁን ላይ የሚጀመሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት እየተጠናቀቁ በመሆናቸው፣ ከተማዋ የነዋሪዎቿን ምቾት እየጠበቀችና የቱሪስት መስህቦቿን እያበዛች የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት የመሆን ፅኑ ጉዞዋን በይፋ ተያይዛዋለች።
ይህ ሰፊ የኮሪደርና የዲጂታል ልማት አዲስ አበባን ንፁህ፣ አረንጓዴና ውብ ሥፍራዎችን የተላበሰች፣ አሠራሯን ያዘመነች እና ሕብረ ብሔራዊነቷ የደመቀባት አስተማማኝ ከተማ አድርጓታል።

ይህም ለዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ሁነቶችና ስብሰባዎች በዋናነት የምትመረጥ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን አብቅቷታል።
ከውበትና ከመሠረተ ልማት ግንባታው ባሻገር፣ ከተማዋ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ባሳየችው ሰው ተኮር የልማት አቅጣጫ የብዙ ነዋሪዎቿን ሕይወት መቀየር መቻሏን የከተማዋ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።
አቅመ ደካሞችንና የተቸገሩትን በመደገፍ፣ ተማሪዎችን በመመገብና በማስተማሪያ ቁሳቁስ በመርዳት፣ የማዕድ ማጋራት መርሐ-ግብሮችን በማስፋፋት እንዲሁም የሸማቾችን የኑሮ ጫና ለማቃለል የተለያዩ የገበያ አማራጮችንና የሌማት ትሩፋት ንቅናቄዎችን በማቅረብ ረገድ አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ መጠጊያና የተስፋ ምንጭ መሆን ችላለች።
በአጠቃላይ የተከናወኑት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መዲናችንን ራሷን እንደ አዲስ የፈጠረችና ለነዋሪዎቿ የምትመች ዘመናዊ ከተማ እንድትሆን አድርገዋታል።