Search

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በካርጎ እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት በዱባይ የዓመቱ ምርጥ ተሸላሚ ሆነ

ዓርብ ሰኔ 05, 2018 49

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት በዱባይ በተካሄደው የ2026 የአቪዬሽን ስኬት ሽልማት ላይ ሁለት ታላላቅ ሽልማቶችን ተሸልሟል።

አየር መንገዱ  በዘርፉ ባሳየው የላቀ ብቃት በአፍሪካ ደረጃ የዓመቱ ምርጥ የካርጎ አየር መንገድ  እና የዓመቱ ምርጥ የኤር ካርጎ ፋርማ አገልግሎት በመሆን ነው የተመረጠው።

በተለይም የፋርማሲዩቲካል (የመድኃኒትና ሕክምና ግብዓቶች) የጭነት አገልግሎት ሽልማቱ፣ አየር መንገዱ ጥንቃቄና ልዩ ቁጥጥር የሚሹ የሕክምና ምርቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ጥራት ለማጓጓዝ ያለውን ተዓማኒነትና ብቃት ያረጋገጠበት ሆኗል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ይህንን ዓለም አቀፋዊ ስኬት አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት፤ ለዚህ ታላቅ ውጤት መገኘት መሰረት ለሆኑት ውድ ደንበኞቹ፣ የንግድ አጋሮቹ እና ሌሊት ከቀን በቁርጠኝነት ለሚሰሩ የሥራ ባልደረቦቹ በሙሉ የላቀ ምስጋናውን አቅርቧል።

ተቋሙ በአህጉሪቱ ያለውን መሪነት ይበልጥ በማጠናከር፣ ወደ ላቀ ከፍታ የመብረርና የመስፋፋት ጉዞውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም  አስታውቋል።