የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የቫቲካን የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ኃላፊ ብፁዕ ወቅዱስ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ እና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሀነኢየሱስ ሱራፌልን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከጳጳሳቱ ጋር ያደረጉት ውይይት እጅግ ፍሬያማና በጋራ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል። በውይይቱ ላይ የሁለቱ ሀገራት ጳጳሳትን ጨምሮ በኢትዮጵያ የቫቲካን አምባሳደር ሊቀ ጳጳስ ብራያን አዳይግዌ ተገኝተዋል።
የቫቲካን የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ኃላፊ ብፁዕ ወቅዱስ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሮቲ እንደገለጹት፤ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ባደረጉት ውይይት የኢትዮጵያ የሥነ-ምግባር እና የሞራል እሴቶች ለሀገራችን ትልቅ ሀብት መሆናቸውን ተገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በጀግኖች የተሞላች፣ የበለፀገ ሃይማኖታዊ ሥነ-ጽሑፍ፣ ምንኩስና እና ሥርዓተ-ቅዳሴ ያሏት ጥንታዊ ሀገር መሆኗን የገለጹት ካርዲናሉ፣ ይህም ጉብኝታቸውን ልዩና አስደሳች እንዳደረገው አብራርተዋል።
አክለውም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ ውስጥ በትምህርት እና በጤና መስኮች ላይ በትብብር እንደምትሰራ ጠቅሰው፤ ይህም የሀገራችንን ተስፋ ሊመጥኑ የሚችሉ የወደፊት ትውልዶችን ለመገንባት ዓላማ ያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በስኬት ያጠናቀቀችውን ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክተው፣ የኢትዮጵያ ጉዞ ሁልጊዜ ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ የማይመለስ በመሆኑ እየታየ ያለው የዲሞክራሲ ዕድገት ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሀነኢየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያና በቫቲካን መካከል ያለው የረዥም ዘመን ታሪካዊ ትስስር በተለያዩ ዘርፎች የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚያሳይ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ከቫቲካን ጋር ያላትን ጠንካራ አጋርነት በመጠቀም፣ በሀገሪቱ ውስጥ የተጀመሩ የልማትና የበጎ አድራጎት ተግባራትን ይበልጥ አጠናክራ እንደምትቀጥልም ብፁዕነታቸው በውይይቱ ወቅት ማረጋገጣቸው ተገልጿል።