Search

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ሁለት ዓመት ከመዋጋት 20 ዓመት መወያየት ይሻላል” ያሉበት ምክንያት

ቅዳሜ ሰኔ 06, 2018 73

ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪኳ ውስጥ በርካታ ውጣ ውረዶችን እና የታሪክ ስብራቶችን አሳልፋለች።

የመደመር እሳቤ እነዚህን ታሪካዊ ስብራቶች ጠግኖ፣ ካለፉት መልካም ተሞክሮዎች በመነሣት እና ስህተቶችን በጥንቃቄ በማረም ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር በምሰሶነት የቆመ ፍልስፍና ነው።

መደመር ከአክራሪ እና ከጠበቡ የማንነት ፖለቲካ አጥሮች በመውጣት፣ ሰፊ እና አካታች በሆነ የሐሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት እንዲገነባ መንገድ ይጠርጋል።

ጦርነት እና ግጭት በዜሮ ድምር ጨዋታ ላይ የተመሠረቱ እና ሁሉንም ወገን ተሸናፊ የሚያደርጉ አውዳሚ መንገዶች ናቸው።

በጠረጴዛ ዙሪያ የሚደረግ እውነተኛ ምክክር ግን እያንዳንዱን ዜጋ እና የፖለቲካ ኃይል እኩል አትራፊ እና አሸናፊ የሚያደርግ ብቸኛው አስተማማኝ ጎዳና ነው።

የመደመር እሳቤ ባለቤት የሆኑት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) "ሁለት ዓመት ከመዋጋት 20 ዓመት መወያየት ይሻላል" የሚለው ታሪካዊ አባባል የዚሁ የምክክር እሳቤ ፍኖተ ካርታ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ሚያዝያ 15 ቀን 2015 . ጦርነት ይብቃ፤ ሰላምን እናፅና በሚል መሪ ሐሳብ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ነበር።

ጦርነት በጥቂት ቀናት ውስጥ የሚያደርሰው ሰብአዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ማኅበራዊ ውድመት ለብዙ አሥርተ ዓመታት የሚዘልቅ ጠባሳ ጥሎ የሚያልፍ ነው። ለዚህ ደግሞ ከኢትዮጵያውያን በላይ ምስክር መጥራት አይቻልም።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አባባል ታዲያ በጠረጴዛ ዙሪያ የሚደረግ እና የቱንም ያህል ረጅም ጊዜ የሚወስድ የሰላም ድርድር ከማንኛውም የኃይል አማራጭ እጅግ የላቀ እና አዋጭ መሆኑን ያስገነዝባል።

በጠመንጃ ኃይል የሚመጣ ዘላቂ ድል እንደሌለ ካለፈው ታሪካችን በላይ ምስክር የለም። ዘላቂ እና አስተማማኝ ድል የሚገኘው ልዩነቶችን በውይይት እና በሐሳብ የበላይነት መፍታት ስንችል ብቻ ነው።

ይህንን የመደመር ሰላማዊ መርሕ በተግባር ለመተርጎም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ሰፊ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የባለድርሻ አካላት ልየታ አጠናቅቆ ለመጨረሻው ምክክር ቀን ቆርጧል።

ይህ የምክክር መድረክ ያለፈ ታሪካችንን በመነቃቀፍ እና በጥላቻ ለመተራመስ ሳይሆን፣ ካለፉት ስህተቶች ተምረን የጋራ እሴቶቻችንን በማጎልበት የምናራምደው የብሔራዊ ሰላም ግንባታ እርምጃ ነው።

መንግሥት ከዚህ ታሪካዊ የጋራ መድረክ የሚፈልቁ የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን ለመቀበል እና በተግባር ለመተርጎም ያለውን ቁርጠኝነት መግለጹ ሂደቱ አዲስ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ያለውን ተስፋ የላቀ ያደርገዋል።

ይህን ወሳኝ የታሪክ አጋጣሚ ለመጠቀም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሰላም እና ለውይይት ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል።

በፍቅር፣ በወንድማማችነት እና በዕውቀት ላይ የቆመውን የመደመር እሳቤ በመላበስ፣ በጦርነት አውዳሚነት ላይ የውይይትን ብርሃን ማብራት ይገባል።

ሁላችንም የሰላም መልዕክተኞች እና የውይይት ጀማሪዎች በመሆን ለነገዋ የበለጸገች እና የተባበረች ኢትዮጵያ የየበኩላችንን አዎንታዊ ዐሻራ ማሳረፍ የዜግነት ግዴታችን ነው።

በለሚ ታደሰ