ለአንድ ሀገር ህልውና መረጋገጥ በዜጎቿ መካከል የሚኖረው የጋራ መግባባት እና ትብብር ከፍተኛውን ሚና ይጫወታል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ውስብስብ ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ፈተናዎች በዘላቂነት ለመፍታት የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር፣ የተዛቡ ትርክቶችን በማረም በይቅርታ ላይ የተመሰረተ መተማመን ለመገንባት ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት መሰረታዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን ማጥበብ የሚቻለው በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ውይይት ብቻ መሆኑን በማመን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ተቋቁሞ ላለፉት አራት ዓመታት የተለያዩ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

በዚህም ሂደት ኮሚሽኑ ባደረገው እንቅስቃሴ 93 በመቶ ከሚሆነው የሀገራችን ክፍል አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ሥራ ማከናወን ችሏል።
ምክክሩ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ በጋራ የሀገር ጉዳይ ላይ መግባባት የመፍጠር አቅም ያለው በመሆኑ እስካሁን በ1 ሺህ 234 ወረዳዎች አሳታፊ የሕዝብ ውይይቶች ተካሂደዋል።
በእነዚህ ወረዳዎች በተደረጉ የምክክር የቅድመ ዝግጅት መድረኮች ላይ ዲያስፖራውን ጨምሮ ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች በቀጥታ የተሳተፉ ሲሆን፣ የሴቶች ተሳትፎም ከ45 በመቶ በላይ ሊደርስ ችሏል።
የማኅበረሳባዊ ቅራኔዎችን በውይይት ከመፍታት ባለፈ ሂደቱ ተቋማዊ መሰረት እንዲኖረው የፌዴራል ተቋማት፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የዚህ ታሪካዊ ሂደት አካል ሆነዋል።
በተጨማሪም ለ8 ሺህ 500 የምክክር አስተባባሪዎች እና አስፈጻሚዎች ሥልጠና ተሰጥቷል።

ይህ አሃዛዊ መረጃ የሚያሳየው ቁርሾ እና ጦርነት ችግሮችን በዘላቂነት እንደማይፈቱ እና የጠረጴዛ ዙሪያ ድርድር ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ የችግሮች መፍቻ ቁልፍ መሆኑን ነው።
የዚህ ሂደት የማጠቃለያ ምዕራፍ የምክክር ጉባኤም ከመላው ኢትዮጵያ በተመረጡ የጉባኤው ተሳታፊዎች በሚገኙበት በመጪው ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ ይጀመራል።
ሀገራዊ ምክክሩ የጥቂት አካላት ሳይሆን የሁላችንም የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወሰንበት መድረክ በመሆኑ ለስኬቱ የበኩላችንን ሚና መወጣት ይጠበቅብናል።
በቢታኒያ ሲሳይ