የአንድ ሀገር ህልውና እና ቀጣይነት ባለው መልኩ መጓዝ የሚወሰነው በዜጎቿ መካከል በሚኖር የጋራ መግባባት እና ትብብር ላይ ነው።
ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ውስብስብ ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ፈተናዎች በዘላቂነት ለመፍታት በአሁኑ ወቅት የጀመረችው ሀገራዊ ምክክር የተዛቡ ትርክቶችን ለማረም እና አዲስ ምዕራፍ የመክፈት ዕድሉ ከፍ ያለ ነው።
ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት ሀገር ብትሆንም በተለያዩ የፖለቲካ ሥርዓቶች ውስጥ እያለፉ እዚህ የደረሱ ማኅበረሰባዊ ቅሬታዎች አሉ።
እነዚህን ማኅበረሰባዊ ቅራኔዎችን ደግሞ በውይይት ከመፍታት ይልቅ በኃይል መደፍጠጥ ልማድ እየዳበረ መጥቶ ኢትዮጵያን መስቀለኛ መንገድ ላይ አቁመዋት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ እነዚህን ያለፉ ታሪካዊ ጠባሳዎች በይቅርታ፣ በውይይት እና በእውነት ላይ በተመሰረተ መተማመን ለመገንባት ዋነኛው መፍትሔ ነው።
በሀገረ መንግሥት ግንባታ፣ በሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያዎች፣ በብሔራዊ ምልክቶች እና በሌሎች መሰረታዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን ማጥበብ የሚቻለው በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ውይይት ብቻ ነው፡፡
ምክክሩ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ በጋራ የሀገር ጉዳይ ላይ መግባባት የመፍጠር አቅም አለው።
በዓለም ታሪክ ውስጥ በትላልቅ የፖለቲካ እና የማኅበረሰብ ቀውሶች ውስጥ ያለፉ በርካታ ሀገራት መሰል ሀገራዊ ምክክሮችን በማካሄድ ወደ ልማት መሸጋገር ችለዋል።
ይህ የሚያሳየው ቁርሾ እና ጦርነት ችግሮችን በዘላቂነት መሆናቸውን፣ የጠረጴዛ ዙሪያ ድርድር ግን ሁሉን አሸናፊ የሚያደርግ የችግሮች መፍቻ የመጨረሻ ቁልፍ መሆኑን ነው፡፡
ከባድ የእርስ በርስ እልቂት ያስተናገደችው ሩዋንዳ ማኅበረሰባዊ ትስስሯን መልሳ የገነባችው ባህላዊ እና ሀገራዊ የውይይት መድረኮችን በመጠቀም ልዩነቷን በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታቷ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ሰሜን አየርላንድ ለሰላሳ ዓመታት የዘለቀውን እና ማኅበረሰቡን ለሁለት ከፍሎ የነበረውን ግጭት በፖለቲካዊ ውይይት እና ድርድር መቋጨት ችላለች።
እነዚህ የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች የሚያሳዩን ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው በኃይል ሳይሆን በሀሳብ የበላይነት ላይ መሆኑን ነው።
ሀገራዊ ምክክሩ የጥቂት አካላት ሳይሆን፣ የሁላችንም የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወሰንበት መድረክ በመሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ ሂደቱን የመደገፍና የበኩሉን አስተዋጽኦ የማበርከት ብሔራዊ ኃላፊነት አለበት።
በሃና ምንዳሁን