Search

በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት በተለያዩ ምክንያቶች ያልተሳተፉ ወገኖች ወደ ምክክሩ እንዲመጡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ

ዓርብ ሰኔ 05, 2018 53

በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ያልተሳተፉ ወገኖች ወደ ምክክሩ እንዲመጡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ፡፡

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ባስተላለፉት በዚህ ጥሪ፤ “እናንተን ተቀብሎ ለማስተናገድ በሩ ሁልጊዜም ክፍት መሆኑን መግለጽ እወዳለሁ” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች በተወካዮቻቸው አማካኝነት ተከባብረው፣ ተደማምጠውና ተመካክረው የሚያቀርቧቸው ምክረ ሐሳቦች በተግባር ተተርጉመው ሀገራችን ወደ አዲስ የሰላምና የእድገት ምዕራፍ እንድትሸጋገር የሁሉም የጋራ ጥረትና ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት ወደ ወሳኝ እና የመጨረሻ ምዕራፍ መሸጋገሩን በይፋ ያበሰረው ኮሚሽኑ፤ የተጣለበትን ታሪካዊ ኃላፊነት በከፍተኛ ታማኝነት፣ ገለልተኝነት እና ቁርጠኝነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን በድጋሚ አረጋግጧል።

ለጉባኤው ስኬታማነት አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ምክክር ተግባራትን ለማከናወን እንዲቻል፣ የተመረጡ ተሳታፊዎች ጉባኤው ከመጀመሩ አንድ ሳምንት ቀደም ብለው ጉባኤው ወደሚካሄድባት አዲስ አበባ ከተማ ተጠቃለው እንዲገቡ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።

በቀጣይ ቀናት ይፋዊ ጥሪና ዝርዝር መረጃዎች በኮሚሽኑ በኩል የሚሰጡ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ እስከዚያው ድረስ ተሳታፊዎች አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ተጠይቋል።

በተጨማሪም ኮሚሽኑ የተጀመረው ታሪካዊ ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን ሕዝቡ፣ መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበራት፣ መገናኛ ብዙኃን፣ የሃይማኖትና የትምህርት ተቋማት እንዲሁም የማኅበረሰብ መሪዎች የተለመደ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠይቋል።