ሀገራት በታሪካቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ውስብስብ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ታሪካዊ ችግሮች ለመፍታት የሚጠቀሙበት የሰለጠነ መንገድ ምክክር ነው።
በጦርነት አሸናፊዎች እና ተሸናፊዎች ሊኖሩ ቢችሉም፣ በውይይት የሚደረስበት መግባባት ሁሉንም የሚያሳትፍና ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣ ነው።
ለዚህም ነው ብዙ ሀገራት በወሳኝ የታሪክ ማጠፊያ ወቅቶች የሀገራዊ ምክክር መድረኮችን የፈጠሩት።
በኢትዮጵያም ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም የሚጀመረው ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከየትኛውም መድረክ በላይ የሆነ ትርጉምን ይዟል። ይህ መድረክ ለዓመታት በሕዝብ ዘንድ ሲነሱ የቆዩ ጥያቄዎች፣ ልዩነቶች እና አመለካከቶች በአንድ ብሔራዊ መድረክ ላይ የሚገናኙበት አጋጣሚ ነው።
በመሆኑም ቀኑ በቀን መቁጠሪያ ላይ የተመዘገበ ቀን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ወደ አዲስ የፖለቲካ ባህል የምትሸጋገርበት ታሪካዊ ምዕራፍም ጭምር ነው።
የዓለም ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች በቀላሉ የሚጀመሩ ቢሆኑም ውጤታቸው ግን የአንድ ሀገርን ታሪክ ሊቀይር ይችላል። በዚህ ረገድ የቱኒዚያ እና የኮሎምቢያ ተሞክሮዎችን ማየት በቂ ነው።
ቱኒዚያ ከፈረንጆቹ 2011 የአረብ አብዮት በኋላ ከባድ ፖለቲካዊ ውጥረት ውስጥ ገብታ ነበር፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በእርስ በርስ ይጋጩ ነበር፣ የሀገሪቱም የወደፊት አቅጣጫ ግልጽ አልነበረም።
በዚያ ወቅት ግን የሠራተኞች ማህበራት፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማት እና የንግድ ማህበራት በመተባበር የብሔራዊ ውይይት መድረክ መፍጠር ቻሉ። ይህ ውይይት ቱኒዚያን ከፖለቲካ ቀውስ አውጥቶ ወደ አዲስ ሕገ መንግሥት እና ወደ ተረጋጋ ሽግግር እንድትገባ አስችሏታል።
የቱኒዚያ ታሪክ የሚያስተምረን ትልቁ ትምህርት ልዩነቶች ምንም ያህል ጥልቅ ቢሆኑም በውይይት መድረክ ውስጥ ሊቀርቡ እና ወደ መፍትሔ ሊለወጡ እንደሚችሉ ነው።
በሌላ በኩል ኮሎምቢያ ለአምስት አስርተ ዓመታት ያህል በተራዘመ የውስጥ ግጭት ቆይታለች፡፡ በዚህም ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ ሚሊዮኖችም ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።
ሆኖም በድርድር እና በሀገራዊ ውይይት ሂደት ውስጥ ተቃራኒ ወገኖች በመገናኘት ወደ ሰላም ስምምነት ሊደርሱ ችለዋል። ኮሎምቢያ የምታስተምረው ደግሞ በጦር ሜዳ ያልተፈቱ ጉዳዮች በውይይት ጠረጴዛ ሊፈቱ እንደሚችሉ ነው።
ኢትዮጵያ ከእነዚህ ሀገራት ጋር በታሪክ፣ በባህል ወይም በፖለቲካ አወቃቀር ተመሳሳይ ባትሆንም ከተሞክሮዎቻቸው የምትወስደው ትልቅ ትምህርት አለ።
ያም የሀገር ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በግጭት ሳይሆን በመነጋገር መሆኑን ነው። በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን በማቋቋም ባለፉት ዓመታት በየደረጃው የዜጎችን ሐሳብ ለማዳመጥና ሁሉን አካላት ያሳተፈ ምክክር ለማከናወን ስትሰራ ቆይታለች፡፡
ይህም ከዜጎች አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት ተጠናቅቆ ዋናውን ሀገራዊ ጉባኤ ለማከናወን ለሐምሌ 8 ቀን ቀጠሮ ተይዟል፡፡ ዕለቱም የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች፣ የማህበረሰብ ክፍሎች እና የትውልድ አመለካከቶች የሚገናኙበት ብሔራዊ መድረክ በመሆን ትልቅ ተስፋ ይዞ ይመጣል።
ከወናው ጉባኤ በኋላ የሚጠበቁ ጉዳዮችም ቀላል አይደሉም፡፡ በኢትዮጵያ የወደፊት ፖለቲካዊ አቅጣጫ፣ የአንድነትና የልዩነት አያያዝ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ የሰላም ማስፈን፣ የተቋማት ጥንካሬ እና የዜጎች የጋራ ራዕይ ግንባታ ላይ አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት ይጠበቃል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ ለዓመታት ሲነሱ የነበሩ ሀገራዊ ጥያቄዎች በተቋማዊ እና በሰላማዊ መንገድ የሚመለሱበትን አዲስ ባህል እንዲፈጥር ተስፋ ተጥሎበታል።
ስለዚህም ሐምሌ 8 ቀን ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ልዩነቶችን ወደ መግባባት፣ ክርክሮችን ወደ ውይይት፣ ውይይትን ወደ ሀገራዊ መፍትሔ የምትቀይርበት ታሪካዊ ዕለት ነው።
ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ምክክር የራሱ ፈተናዎች ቢኖሩትም ሀገራትን ከክፍፍል ወደ መግባባት፣ ከግጭት ወደ ሰላም፣ ከጥርጣሬ ወደ የጋራ ራዕይ ሊወስድ የሚችል መሣሪያ ነው።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ