Search

የምርጫው ሂደት ለሰለጠነ የሀሳብ የበላይነት ያለንን ዝግጁነት ያሳየንበት ነው - የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ

እሑድ ሰኔ 07, 2018 43

የኢትዮጵያ ሕዝብ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሚሊዮኖች በመመዝገብና በፅናት በመምረጥ ለሀገሩ ያለውን ፍቅርና ለዘላቂ ሰላም ቀናዒነቱን በተግባር አስመስክሯል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።

ፕሬዚዳንቱ ይህን የገለጹት የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለተሳተፉና አዎንታዊ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሲቪል ማኅበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን ባዘጋጀው ሀገር አቀፍ የዕውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር ላይ ነው።

ፕሬዚዳንት ታየ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከቅድመ ምርጫ እስከ ምርጫው ዕለት በኢትዮጵያዊ ስክነት በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው አልፎ ለዓለም ውህደትና ልማት መሠረት የሆኑ የጥንታዊ ሀገር በቀል እሴቶች ባለቤት መሆናቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህ የኢትዮጵያ እሴት ግን ተገቢው የፖለቲካ ልምድ ታክሎበት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዳይሸጋገር የነፍጥ ትግል እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አስገንዝበዋል።

በዚህም በውይይት፣ በንግግርና በሀሳብ ልዕልና ሊፈቱ የሚችሉ ልዩነቶችን በኃይል ለመፍታት በመሞከሩ የዴሞክራሲ ሂደቱ ፈታኝ ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰዋል። 

በመሆኑም ከታሪካዊ ሥልጣኔያችን አኳያ የተመኘነውን ያህል መራመድ ባንችል እንኳ፣ ያለፈውን ስህተት አርመን የተሻለች ሀገር ለመገንባት ቁጭታችንን ስንቅ ልናደርግ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ከቅድመ ምርጫ እስከ ድህረ ምርጫ ባለው ሂደት ፍትሐዊና ሰላማዊ መንገድን በመከተል፣ ለዘመናዊ መንግሥት ግንባታ ፍትሐዊ ምርጫ ቁልፍ መሆኑን በተግባር ማሳየታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ተስፋ የሚለመልመው በሰለጠነ ምርጫ ነው በሚል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በነቂስ ወጥተው በመምረጥ የነውጥ፣ የጥፋትና የሞት ድግስን ማክሰም ችለዋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ሕዝቡ በትዕግሥት ድምፁን በመስጠት የሀገሪቱ ዕጣ ፈንታ በእጁ መሆኑን በአሻራው ማተሙን ተናግረዋል።

ለሕግ የበላይነት መገዛት፣ ውይይትና ንግግር የሰለጠነ ፖለቲካ መገለጫዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የምርጫው ሂደት ለሰለጠነ የሀሳብ የበላይነት ያለንን ዝግጁነት ያሳየንበት ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ምርጫ በጥቂት ልሂቃን መካከል የሚደረግን ውድድር ለመታዘብ ሳይሆን ዘላቂ ሰላምን ለማፅናት የሚደረግ የዴሞክራሲ መንገድ መሆኑን አብራርተዋል።

 

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የጎላ አበርክቶ ላደረገው ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለጸጥታ ኃይሎችና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ፕሬዚዳንቱ ምስጋና ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

"የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ያመሰግናሉ" በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀው በዚህ መርሃ ግብር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ፣ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፣ ሚኒስትሮች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።