Search

የተፈጥሮ ጥሪና የእያንዳንዳችን ዐሻራ

እሑድ ሰኔ 07, 2018 55

አረንጓዴ ሕይወት ከሰው ልጅ መኖርና ደህንነት ጋር የማይነጣጠል ጥልቅ ትስስር አለው። ተፈጥሮ ንጹህ አየርን፣ ዝናብንና ለምለም መሬትን በመለገስ የሰውን ልጅ ህልውና ስትደግፍ፣ ሰው ደግሞ እሷን በመንከባከብና በመጠበቅ ውለታዋን ይመልሳል።

ይህ በእንክብካቤ ላይ የተመሠረተ የጋራ መስተጋብር የሕይወት ቀጣይነት መሠረት ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ይህንን እውነታ በተግባር በማሳየት ረገድ ተጠቃሽ ታሪካዊ ስኬትን ማስመዝገብ ችላለች።

ሀገራችን በጀመረችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አማካኝነት ባለፈው ዓመት ብቻ 7.5 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል የቻለች ሲሆን፣ በተለይም በአንድ ጀምበር 615 .7 ሚሊዮን ችግኞችን አፈር በማልበስ የተከናወነው አኩሪ ተግባር የሕዝባችንን የአንድነት ኃይልና ለተፈጥሮ ያለውን የጋራ ጽናት ያሳየ ደማቅ ዐሻራ ሆኖ አልፏል።

ይህ ታላቅ ስኬት በቃላት ጌጥ የሚገለጽ ሳይሆን፣ በዐይን በሚታይ የደን ሽፋን ዕድገትና በተደራሽ የአካባቢ ሥነ-ምህዳሮች መታደስ የሚመሰከር እውነተኛ ለውጥ ነው።

ይህንን መልካም ጅምር ይበልጥ ለማስቀጠልና የነገዋን ውብ ኢትዮጵያን ለማብሰር ዘንድሮ ደግሞ ተጨማሪ 8 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታላቅ ግብ ተቀምጧል።

ይህ ዕቅድ የዛሬውን ትውልድ ፍላጎት ከመሙላት ባለፈ፣ ለቀጣዩ ትውልድ የተደላደለች፣ ለምለምና አረንጓዴ ሀገርን ለማውረስ የሚደረግ ትርጉም ያለው ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው።

እያንዳንዷ የምንተክላት ችግኝ የተስፋ ጭላንጭል እንደመሆኗ መጠን፣ ሁላችንም የተፈጥሮን ጥሪ በመቀበል፣ ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ አረንጓዴ ሕይወትን ከራሳችን ሕይወት ጋር እናስተሳስር።

በማስተዋል መታፈሪያ