(የዕለቱ መልዕክት)
ተፈጥሮ በለመለመ እቅፏ አውርሳን የነበረችውን ድንቅ ምድር፣ ዛሬ በእኛ እጅ ውበቷ እንዳይደበዝዝ ታላቅ አደራ ከፊታችን ተደቅኗል።
ኢትዮጵያ ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የዛሬ ሰባት ዓመት የጀመረችውን የአረንጓዴ ዐሻራ በጎ ተግባር አስቀጥላለች።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የሀገራችንን የነገ ዕጣ ፈንታ የሚወስን፣ ጊዜውን የዋጀ እና ትውልድን የሚታደግ ብሩህ ጎዳና ነው።
ይህ ንቅናቄ ተባብረን እና ተጋምደን ሀገራችንን ከቀውስ የምንታደግበት፣ የትናንት የነጻነት ዐርበኝነታችንን በተፈጥሮ ጥበቃ የምንደግምበት የዘመናችን ድንቅ ዓድዋ ነው።
ይህ የዘመናችን ዓድዋ ደግሞ የዛሬውን “የመደመር ትውልድ” የታሪክ ዐሻራ እና ሁለንተናዊ አቅም የሚፈትን ታላቅ ሀገራዊ ጥሪ ነው። ትናንት አባቶቻችን ልዩነቶቻቸውን አክስመው በዓድዋ ዓውድማ ላይ በአንድነት ለነጻነት እንደቆሙ ሁሉ፣ የዛሬው የመደመር ትውልድም ዕውቀቱን፣ ጉልበቱን እና ፍቅሩን አስተባብሮ ለሀገራችን አረንጓዴ ልብስ ሊያለብሳት ይገባል።
ይህንን ታላቅ ሀገራዊ ራዕይ ከዳር ለማድረስ ሰፊ ጉልበት እና አቅም ያለው የመላው ኅብረተሰብ ንቁ ተሳትፎ ያስፈልጋል።
የባለቤትነት ስሜት በሁላችንም ልብ ውስጥ ይበልጥ እንዲያብብ እና አረንጓዴው ዐሻራ እንዲያፈራ፣ ሥራው በወል መሬት ላይ ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ዜጋ የግል ይዞታ እና ደጃፍም ጭምር መተግበር አለበት።
እያንዳንዷ በየቤታችን የምንተክላት ችግኝ ነገ ተያይዛ ታላቅ ደን፣ ታላቅ ሀገራዊ ኃይል ትሆናለች። ዛሬ በእኛ በመደመር ትውልድ ትከሻ የምናደርገው ጥረት ሀገራችን የምግብ ዋስትናዋ በዘላቂነት የተረጋገጠ እና የአየር ንብረት መዛባት የማይበግራት ጽኑ እንድትሆን ያደርጋታል።
የደን ልማት አካል የሆነው ይህ በጎ ተግባር ከሀገራዊ ፋይዳው ባሻገር፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ በረከቶችን እና ሰላምን የተሸከመ የሕልውናችን መሠረት ነው። \
ለሀገራችን የደን ልማት የቅንጦት ወይም የውበት ጉዳይ ሳይሆን፣ በቀጥታ ከሕልውና ጋር የተያያዘ ቁልፍ ጉዳይ ነው።
በዘንድሮው አረንጓዴ ዐሻራ መሪ ቃላችን እንደተመላከተው “ተስፋን እንትከል”! አዎ፣ ዛሬ የምንተክላት እያንዳንዷ ችግኝ ለነገው ትውልድ የምናበረክታት የሕይወት፣ የሰላም እና የብልጽግና ተስፋ ናት።
ይህ ተግባር የመጪው ትውልድ ድንቅ ቅርስ እና የማያረጅ ውርስ ነው። “እናት ሙታ ልጅ አታሳድግም” እንደሚባለው ሁሉ፣ የተራቆተች እና የደረቀች ምድርም የነገ ልጆቿን ልታቅፍ፣ ልትመግብ እና ልታሳድግ አትችልም።
ስለዚህ ነገ በታሪክ እና በትውልድ ፊት እንዳናፍር፣ የለመለመች እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማየት ዛሬ ሁላችንም በጋራ ልንነሣ እና ታሪካዊ የዓድዋ ድላችንን በአረንጓዴ ልማት ልንደግመው ይገባል።
እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉን አረንጓዴ ዐሻራ በማሳረፍ ተስፋን ይትከል፤ ለተተኪው ትውልድ የሚበቅል፣ የሚለምልም እና የሚጠቅም ሕያው ቅርስ ያውርስ። የተስፋችን ምድር ትለምልም።
የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል