የሰው ልጅ የታሪክ ጉዞ የሥልጣኔ፣ የጥበብ እና አብሮ የመኖር እሴቶች ድምር ውጤት ነው። ከእነዚህ የሥልጣኔ ከፍታዎች መካከል ደግሞ ዋነኛው የሀገረ መንግሥት ግንባታ ነው። የሀገረ መንግሥት ግንባታ የዘመናዊ ፖለቲካዊ ማኅበረሰብን መሥፈርቶች የሚያሟሉ ጠንካራ ተቋማትን መፍጠርን ይጠይቃል።
ይህ ሂደት አንድ የጋራ ሕዝብ የሚያልፍበት ታላቅ የላዕላይ መዋቅር ነው። ተቋማት ስንል የፍትሕ ሥርዓቱን፣ ሕገ መንግሥቱን እና የፖለቲካ አደረጃጀቶችን ያካትታል። የመንግሥትና የአስተዳደር ቅርጽን፣ እንዲሁም የቡድንና የግለሰብ መብቶችን በሚዛን አቅፎ የያዘ ትልቅ የሕዝብ ጥላ ነው።
ወደ ሀገራችን ነባራዊ እውነታ ስንመጣ፣ ኢትዮጵያ ረጅም የመንግሥትነት ታሪክ ያላት ጥንታዊት ሀገር መሆኗ አይካድም። ይሁንና ይህን ታላቅ መዋቅር በተሟላ ሁኔታ የመገንባቱ ታሪካዊ ጉዞ አልጋ በአልጋ አልነበረም።
በብዙ እንከኖች የተሞላና አስተማማኝ መሠረት ያልተጣለበት መሆኑ፣ ዛሬ ላይ ከባድ የታሪክ ዕዳ ሆኖብናል።
"ኢትዮጵያ ለምን የተጨናገፈ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት አጋጠማት?" ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። የዚህ ሀገራዊ ፕሮጀክት መክሸፍ ዋነኛ ምክንያት፣ ጽንፍ የያዙ ነጠላ ትርክቶች መፈጠራቸው ነው። ከታሪክ እውነታ ይልቅ፣ ትርክቶቹ የፖለቲካ ንትርክ መሠረት ሆነው እስከ ዛሬ ዘልቀዋል።
ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያን በዋልታ ረገጥ የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ሲንጣት ቆይቷል። በእነዚህ የተራራቁ ትርክቶች ሳቢያ፣ አገራዊነት (Statehood) የሚባለው የጋራ ስሜት በአስተማማኝ ሁኔታ አልተገነባም። ሰፊ መዋቅራዊ ስብራትም አጋጥሞናል።
ይህንን በትርክት ማዕበል ሲናጥ የቆየ ጉዞ ማከም የግድ ይላል። እንደ ዘርፉ ምሁር ጆቼን ሂፕለር አገላለጽ፣ ስኬታማ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሦስት አካታች ምሰሶዎችን ይፈልጋል። የመጀመሪያው ሕዝቦች የጋራ ማንነታቸውን የሚረዱበት 'የወል ትርክት' መገንባት ነው።
ሁለተኛው ሰዎችን በተጨባጭ የሚያስተሳስር መሠረተ ልማት፣ የሐሳብ ልውውጥ እና የምጣኔ ሀብት ትስስርን ማጎልበት ነው። ሦስተኛው ደግሞ ጠንካራ ተቋማዊ አቅም መዘርጋት ነው። ሀገራዊ ምክክር እነዚህን ሦስት ምሰሶዎች በአንድ የውይይት ጠረጴዛ ዙሪያ ያመጣል።
የሀገረ መንግሥት ግንባታውን ሂደት በማሳለጥም ህዝብን ወደ ላቀ የሥልጣኔ ከፍታ ያሸጋግራል።
ሀገራዊ ምክክርን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም አንጻር ስንፈትሸው፣ ለሀገሪቱ ህልውና ወሳኝ ድልድይ መሆኑን እንረዳለን። ከተመካከርን በእርግጥም እንሻገራለን።
ለልጆቻችን የምትተርፍ ጠንካራ ሀገር እናቆያለን። ትውልዳዊ ኃላፊነታችንንም እንወጣለን። ይህ መመካከር በቀላሉ የማይገኝ፣ በስስት ልንመለከተው የሚገባ ታላቅ ዕድል ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይህንኑ ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ሠፊ ኃላፊነት ወስዶ እየሠራ ይገኛል።
ከዝግጅት ምዕራፍ አንስቶ አጀንዳ እስከ ማሰባሰብ ዘልቋል። አራት ሺህ የሚጠጉ ከወረዳ፣ ከክልል፣ ከፌዴራልና ከዳያስፖራ የተውጣጡ ወኪሎችን አሳትፏል። ተፎካካሪ ፍላጎቶች ባሉባት ሀገር፣ ሁሉም ፍላጎቱን በሰላማዊ መንገድ የሚያንጸባርቅበትን የዴሞክራሲ ተቋማዊ ጥራት ለማሻሻል ጽኑ መሠረት እየጣለ ነው።
ታሪክን ወደ ኋላ እየሄዱ መቆስቆስ እና አሁን ላለንበት ሁኔታ ፈራጅ ማድረግ ጉዳት እንጂ ትርፍ የለውም። ታሪክን በታሪክነቱ ተምረን፣ በጎውን ነቅሰን ለነገ ስንቅ ማድረግ አለብን። ይህ የብሔራዊ ጥቅማችን ቀዳሚ መርህ ሊሆን ይገባል።
መመካከር ማለት የራስን ሐሳብ በሌላው ላይ በኃይል መጫን አይደለም። ይልቁንም የጋራ እውነትን ፍለጋ በአክብሮትና በክፍት ልቦና አብሮ መጓዝ ነው።
ትናንት ያለፍንበት መንገድ ዛሬ ለብዙ ጭቅጭቆች መነሻ ሆኗል። አገራዊነት የሚባለው የጋራ ስሜት እንዲገነባ ከተፈለገ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን መገንባት የግድ ነው። ይህ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል።
ሀገራዊ ምክክር፣ በነጠላ ትርክት ስትናጥ የቆየችውን መርከብ ወደ ጸጥታው ወደብ ያሻግራል።
በንዑሳን ማንነቶች እና በአገራዊ አንድነት መካከል ያለውን ሚዛን ያስጠብቃል። የጋራ አገራዊ ማንነትን በውይይት የመፍጠር ትውልዳዊ ተግባር ነው።
የሀገሪቱ የለውጥ እሳቤዎች ወደ ተግባር ሊቀየሩ ይገባል። ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን እንዲጸና፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠን ለመነጋገር መቁረጥ አለብን። ይህ የሁሉንም አካል የላቀ ቁርጠኝነትና ትጋት የሚጠይቅ የታሪክ ቅዱስ ጥሪ ነው!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ