Search

የተስፋው ትውልድ አሻራ፡ ከሀገራዊ ራዕይ እስከ ዓለም አቀፍ ልዕልና

እሑድ ሰኔ 07, 2018 47

ሀገር ማለት የትናንት ታሪክ፣ የዛሬ ጥረት እና የነገ ተስፋ ድምር ውጤት ናት። ዛሬ የምናሳርፈው እያንዳንዱ አሻራ ለነገው ትውልድ የምናወርሰው የእድገት እና የሰላም ተሥፋ ነው። 

2011 . በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መሪነት ይፋ የተደረገው የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲስ ሀገራዊ እይታ መፍጠር ችሏል። የኢትዮጵያ መንግስት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ላይ የወሰደው ቁርጠኝነት የሚመነጨው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ "መደመር" ዕሳቤ ነው።

ይህ ዕሳቤ በአረንጓዴ አሻራ በተግባር ሲተረጎም አካባቢን፣ ኢኮኖሚን እና ብሔራዊ ማንነትን በማዋሃድ አዲስ ዓይነት ስነ-ምህዳራዊ የመንግስት አስተዳደር እንዲፈጠር አድርጓል።

ታሪክ ሰሪው የመደመር ትውልድ ደግሞ ይህንን የሀገር ውስጥ ራዕይ ይዞ በመነሳት፣ ታላላቅ ሀገራዊና አህጉራዊ ብሎም ዓለምአቀፋዊ ጉዳዮችን በብቃት እየከወነ ይገኛል።

የአረንጓዴ አሻራ ጉዳይ አንድምታው ከችግኝ ተከላ የዘለለ መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ያለው ይህ ትውልድ፣ የራሱን አቅምና ሁለንተናዊ ብቃት በዓለም አደባባይ እያስመሰከረ ነው።

የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የትናንት የነጻነት አርበኝነታችንን በተፈጥሮ ጥበቃ የምንደግምበት የዘመናችን ድንቅ «ዓድዋ» ነው። ይህ የዘመናችን አድዋ ደግሞ የዛሬውን «የመደመር ትውልድ» የታሪክ አሻራ እና ሁለንተናዊ አቅም የሚፈትን ታላቅ አገራዊ ጥሪ ነው።

የዛሬው የመደመር ትውልድ እውቀቱን፣ ጉልበቱንና ፍቅሩን አስተባብሮ በተከታታይ ዓመታት አገሩ አረንጓዴ እያለበሳት ይገኛል። ዛሬ በእኛ (በመደመር) ትውልድ ጥረት እየተሰራ ያለ ስራ አገራችን የምግብ ዋስትናዋ በዘላቂነት የተረጋገጠና የአየር ንብረት መዛባት የማይበግራት ጽኑ እንድትሆን ያደርጋታል።

"የችግኝ ተከላ ተግባራችን ስለ ዛፎች ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱ ለትውልድ ጥላ እና ተስፋን ስለመፍጠር ነው።" የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መርህ በመከተል እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ የዘመናችንን ሜጋ ፕሮጀክቶች ከደለል የሚታደግ፣ በግብርናው ዘርፍ የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ፣ በኢንዱስትሪው ለሚፈጠሩ የግብርና ማቀነባበሪያዎች ጥሬ ዕቃ የሚያቀርብ እና በአጠቃላይ በኢኮኖሚ, በልማት እና በማህበራዊ ስነ-ልቦና ላይ ጠንካራ መሠረት የሚጥል ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ ነው።

ይህም የመደመር ትውልድ የተፈጥሮ ሚዛንን ከመጠበቅ ባሻገር ሀገራዊ የልማት ምሰሶዎችን እንዴት ማፅናት እንደሚቻል ያሳየበት ህያው ማረጋገጫ ነው።

"ተስፋን እንትከል" ሲባል መሬት ላይ ችግኝ ማፅደቃችን ብቻ ሳይሆን፣ በልጆቻችን እና በቀጣዩ ትውልድ አዕምሮ ውስጥ የሀገር ፍቅርን፣ አብሮነትን እና የማይበገር ጥንካሬን መዝራታችን ነው።

የትናንት ታሪካችን የቱንም ያህል በፈተናዎች የተሞላ ቢሆንም ዛሬ የመደመር ትውልድ በእጆቹ የሚተክለው ተስፋ፣ ለነገው ትውልድ የማያልፍ ጥላ፣ የማይነጥፍ የኢኮኖሚ በረከት እና ቀና ብሎ የሚኮራባት ቅርስ ሆኖ ይፀድቃል። ስለዚህ ተስፋችንን እንትከል፤ የነገዋን ብሩህ ኢትዮጵያ ዛሬ በጋራ እንገንባ!

በበረከት ሽመልስ