Search

ጀግናዋ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የረዳት ኮሚሽነርነት ማዕረግ አገኘች

እሑድ ሰኔ 07, 2018 42

የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የስፖርት ክለብ እንዲሁም የሙዚቃና ቴአትር ቡድን የተመሠረተበት 40 ዓመት ክብረ በዓል በአድዋ ድል መታሰቢያ በድምቀት ተከብሯል።

በዚሁ መድረክ ላይ በኦሎምፒክና በዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች በርካታ ሜዳሊያዎችን በማምጣት የሀገርን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ላደረገችው ጀግናዋ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የተቋሙ ከፍተኛ የዕድገት እርከን የሆነው የረዳት ኮሚሽነርነት ማዕረግ ተሰጥቷታል።

በዕለቱም ለረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን፣ ለኮማንደር ፋጡማ ሮባ፣ ለኮማንደር አትሌት ሰለሞን ባረጋ እና ለምክትል ኮማንደር ሰንበሬ ተፈሪ የዕውቅናና ሽልማት ፕሮግራም ተካሂዷል።

በተጨማሪም በአሰልጣኝነት 30 ዓመታት በላይ በማገልገል የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱት ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሸቦ የኒሻን ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን፤ በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ ለሀገር ትልቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሙዚቃና ቴአትር ቡድኑ አባላትም ዕውቅና ተሰጥቷል።

በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የፍትሕ ሚኒስትር ሐና አርዓያሥላሴ የኮሚሽኑ የስፖርት ክለብ ባለፉት 40 ዓመታት እውቅ ጀግኖችን በማፍራት በኩል የላቀ ሚና መጫወቱን ጠቅሰው፤ ተቋሙ ይህንኑ አበረታች ሥራውን ይበልጥ ዘመናዊ በማድረግ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።

በበኩላቸው ኮሚሽነር ጄኔራል የኑስ ሙሉ ተቋሙ ታራሚዎችን አምራችና ሕግ አክባሪ ዜጋ አድርጎ የማውጣት ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸው፤ ይህንንም ለማሳካት የስፖርት እና የኪነ-ጥበብ ክፍሎቹ ታራሚውን በማዝናናት፣ በማስተማርና የአካል ብቃት በማጎልበት በኩል ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወቱ መሆኑን አስታውቀዋል።