Search

የመደመር ትውልድ፦ የታሪክን አዙሪት የቀየረና ተፈጥሮን እያከመ ያለ ትውልድ

እሑድ ሰኔ 07, 2018 50

ዘመናት ተፈራርቀው፣ የታሪክ ገጾች በተገለጡ ቁጥር አዳዲስ ትወልዶች የራሳቸውን ድርሳን ይፅፋሉ። ትውልድ የሚለካው በዘመኑና በራሱ አውድ ቢሆንም ሁሉም ትውልድ እንደ ተልዕኮው መጠን ግን መመዘኑ አይቀርም።

በኢትዮጵያ የተነሳው የመደመር ትውልድ ግን ከኖረበት ዘመን የተሻገረ ያለፉትን ትውልዶች እዳ እያወራረደ ጭምር ታላቅ የድል ትርክትን እየገነባ፣ የታሪክ አዙሪትን እየቀየረ፣ በኢትዮጵያ ምድር አዲስና ልዩ እውነታን እየከሰተ ያለ ትውልድ ሆኗል።

ኢትዮጵያ ለዘመናት ያራቆታትን የተፈጥሮ መመናመን ሕመም፣ ይህ የመደመር ትውልድ "አረንጓዴ አሻራ" መድኃኒትነት እየፈወሰው ነው። ተራሮች ዳግም አረንጓዴ ካባ ሲለብሱ፣ የደረቁ ምንጮች ውሃ ሲያመነጩ፣ ይህ ትውልድ በክረምት ዝናብ ሳይበገር፣ በበጋ ሀሩር ሳይበገር በማዕበል ወጥቶ ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የተፈጥሮን ሚዛን መልሶ ጠብቋል።

ቆፈን እና ድርቅ ያጠወለገውን የሀገሪቱን ገጽታ፣ በፍቅር እና በላብ አርሶ፣ በምስራቅ አፍሪካ ምድር ላይ ለትውልድ የሚሻገር የህይወት ኦክስጅንን እየተነፈሰ ነው። ይህ አረንጓዴ ንቅናቄ የመሬትን ድርቀት እና የልምላሜ እጦት ከመፈወስ አልፎ፣ የአብሮነትን እና የህብረትን ስነ-ልቦና ያከመ ታላቅ የትውልዱ ማህተም ሆኖ በደማቁ ተጽፏል።

በመደመር ፍልስፍና የታነጸው ይህ ትውልድ፣ የኢትዮጵያን የዘመናት የድህነት እና የልመና ታሪክ በመቀልበስ የኢኮኖሚ ስብራቷን እያጠገነ ይገኛል። መሬት ቧጥጦ፣ በበጋ ስንዴ ልማት ተዓምር ሰርቶ፣ "ከእጅ ወደ አፍ" ከሆነ የዕለት ጉርስ ትርክት ወጥቶ ሀገርን ወደ ምርት ላኪነት አሸጋግሯል።

ጠላቶቿ "በጭለማ ትኑር፣ ከውሃዋ አትጠቀም" ብለው የሸረቡትን ሴራ በጥበብ አክሞ፣ የውሃ በሮቻችንን ዘግቶ፣ ግድቦቻችንን በራሳችን አቅም ገንብቶ፣ ለዘመናት በጨለማ የኖሩ መንደሮችን በብርሃን እያጥለቀለቀ ነው።

በገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለትውልድ እና በሌሎችም ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች፣ የሀገሪቱን ድብቅ ውበቶች ፍንትው አድርጎ በማውጣት ኢትዮጵያን የተፈጥሮ እና የሰው ሰራሽ ቱሪዝም ማዕከል አድርጓታል። ጎርጎራ፣ ኮይሻ፣ ወንጪ፣ ሀላላ ኬላ እና የሸገር ከተማ ግንባታዎች የዚህ ትውልድ የእጅ ስራዎች፣ የሀገርን የልማት ህመም ያከሙ የብልፅግና ማሳያዎች ናቸው።

ይህ ትውልድ የኢትዮጵያን እንባ አብሷል። በድህነትና ኋላቀርነት ጭራ ሆና የነበረችውን እናት ሀገሩን በትጋቱ፣ በላቡ፣ በእውቀቱ እና በፍቅሩ አክሟል። ተስፋ በመቁረጥ እና በማማረር ፈንታ፣ አካፋ እና ዶማ አንስቶ ሀገርን ገንብቷል።

"ኢትዮጵያን ያከመ የመደመር ትውልድ" ተብሎ በታሪክ መዝገብ ላይ በወርቅ ቀለም ስሙ ለዘላለም ይሰፍራል። የነገዋ ኢትዮጵያም፣ ዛሬ በተዘራው የመደመር ዘር፣ አረንጓዴ ለብሳ፣ በኢኮኖሚ በልጽጋ፣ በልጆቿ አንድነት አሸብርቃ፣ በአለም አደባባይ ደረቷን ነፍታ ትቆማለች።

ይህ የመደመር ትውልድ የችግር ሰለባ ከመሆን ወጥቶ፣ የመፍትሄው ባለቤት በመሆን፣ የኢትዮጵያን ትንሳኤ በተግባር እያረጋገጠ ያለ የተስፋ ብርሃን እና የሀገር ጠባቂ ሐኪም ነው። የጀመረው ፈውስ ሙሉ እስኪሆን ድረስ፣ በእልህ እና በቁርጠኝነት የብልጽግናዋን ጫፍ ለማየት ጉዞውን ቀጥሏል።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ