የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላለፉት አራት ዓመታት አጀንዳዎችን በማሰባሰብ እና ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ያካተቱ ተወያዮችን በመለየት ያካሄደውን ሰፊ የዝግጅት ምዕራፍ አጠናቅቋል።
የመጨረሻውን እና ወሳኙን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለማካሄድም ለሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል።
ይህ ታሪካዊ መድረክ የፖለቲካ ኃይሎች እና የኅብረተሰብ ክፍሎች መሰባሰቢያ ተራ መድረክ አይደለም።
ይልቁንም ሀገራችን ለዘመናት የተሸከመችውን ውስብስብ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ መስተጋብር ስብራቶች በመጠገን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የምትከፍትበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው።
የዚህ ምክክር በስኬት መጠናቀቅ በተለይም ጠንካራ ሀገረ መንግሥትን ከማጽናት እና ነጻ ተቋማትን ከመገንባት አኳያ የሚኖረው ትርጉም እጅግ የላቀ ነው።
ሀገረ መንግሥት በጽኑ መሠረት ላይ ሊቆም የሚችለው ዜጎች በሀገራቸው ብሎም በመንግሥታዊ መዋቅሩ ላይ የጸና እምነት እና የጋራ መተማመን ሲኖራቸው ነው።

ሀገራዊ ምክክሩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና የፖለቲካ ልሂቃን መሠረታዊ ልዩነቶቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ በሰለጠነ መንገድ እንዲፈቱ ያስችላል።
ከዚህም ባለፈ ለዘመናት የዘለቀውን የጠላትነት እና የመጠራጠር መንፈስ ወደ መተማመን እና መግባባት ይለውጠዋል።
ይህ አካታች ሂደት ታሪካዊ ቁስሎችን በማዳን እና ሀገራዊ ራዕይን በማጋራት፣ ሕዝቡ በሀገረ መንግሥቱ ሕልውና ላይ ያለውን የባለቤትነት ስሜት በእጅጉ ያሳድገዋል።
ልዩነቶችን አቻችሎ ማኅበራዊ ትስስርን በማጠናከር እና ለኢትዮጵያ የሚበጅ አዲስ ማኅበራዊ ውል በመፍጠር ረገድ የምክክሩ ስኬት የማይተካ ሚና አለው።

ከመተማመን ባሻገር የምክክሩ ስኬት በቀጥታ የሚተረጎመው አቅም ባላቸው፣ ገለልተኛ በሆኑ እና በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒነትን ባተረፉ ጠንካራ ተቋማት ግንባታ ነው።
በምክክሩ ሂደት የሚደረሱ የፖለቲካ እና የሕግ ስምምነቶች የዴሞክራሲ፣ የፍትህ እና የአስተዳደር ተቋማትን ነጻነት የሚያረጋግጡ የለውጥ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣሉ።
ግጭቶችን በጉልበት ከመፍታት ይልቅ በሕግ የበላይነት እና በውይይት የመፍታት አዲስ የፖለቲካ ባህል በመትከል፣ ተቋማት ከግለሰቦች ተጽዕኖ ነጻ በመሆን የሀገርን እና የሕዝብን ጥቅም ብቻ መሠረት አድርገው እንዲያገለግሉ ያግዛል።
የፍትህ፣ የጸጥታ እና የአስተዳደር ተቋማት ጠንካራ እና አሳታፊ ሆነው ሲገነቡ የሀገረ መንግሥቱ ግንባታ የጀርባ አጥንት ይሆናሉ።
በመሆኑም በቀጣይ የሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር ኢትዮጵያ ጠንካራ ተቋማትን በማነጽ እና የዜጎችን መተማመን በማረጋገጥ ወደማትናወጥ፣ ሉዓላዊነቷ እና አንድነቷ ወደተረጋገጠ ሀገረ መንግሥት የምታደርገው የተስፋ ጉዞ ቁልፍ ምዕራፍ ነው።
በለሚ ታደሰ