7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለዴሞክራሲያዊና ለሲቪል የፖለቲካ ባህል መጎልበት የፈጠርነውን ምቹ ምህዳርና ተቋማዊ አቅም ያሳየ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ጋር በመሆን፣ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መሳካት ጉልህ አስተዋፅኦ ላበረከቱና በቁርጠኝነት ለተጉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ባለድርሻ አካላት የተዘጋጀውን የዕውቅና መርሃ ግብር ታድመዋል።
በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጉዞ ጉልህ አሻራ ባሳረፈው በዚህ ምርጫ የሥልጣን ሽግግርና የፖለቲካ ፉክክር በሰላማዊ መንገድና በምርጫ ብቻ መሆኑን በማሳየት ረገድ የሲቪል ማህበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች የተጫወቱት ሚና የላቀ ነው ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ ዘላቂ ሰላምና የዴሞክራሲ ባህል የጎለበተባት ኢትዮጵያን የመገንባት ዓላማ አንግበን እየሠራን እንገኛለን ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፌስቡክ የማኅበራዊ ትስስር ገፅ ባሰፈሩት መልዕክት።
በዚህ ሂደት የሲቪልና የፖለቲካ ድርጅቶችን ተቋማዊ አቅም ለማጠናከርና ምህዳሩን ይበልጥ ለማስፋት መንግሥት የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።