Search

ምክክር፦ ብቸኛው የፈተናዎቻችን ማለፊያ

እሑድ ሰኔ 07, 2018 37

ኢትዮጵያ በዘመናት ፈተና ውስጥ አልፋ ለዛሬ የደረሰችው በሕዝቦቿ ልዩ መስተጋብር እና ጥብቅ አንድነት ነው።

ታሪካችንን ወደኋላ ስንቃኝ በሕብረት ጦርነቶችን አሸንፈን የጋራ ነጻነታችንን ያስከበርን፣ በአንድ መሶብ ዙሪያ ከብበን በጋራ የበላን፣ "እኔ ልደፋልህ/ልደፋልሽ" መባባልን የመሰለ ድንቅ ባህል ያዳበርን ሕዝቦች ነን።

ሀገር በባዕዳን ተደፈረች ሲባል የውስጥ ልዩነታችንን ወደ ጎን ትተን ወደ ጦር ሜዳ የተመምነው እና ኢትዮጵያን በፈተናዎች ውስጥ ጠብቀን ያኖርነው በዚህ የጋራ ሥነ-ልቦና ነው።

ይሁን እና ይህ ሁሉ ታሪክ እያለን ዛሬ ላይ "በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለን በመመካከር ችግሮቻችንን መፍታት ለምን ተሳነን?" የሚለው ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ የሚሻ ጉዳይ ነው።

የዘመናዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አመጣጥ ከታሪካዊ እሴቶቻችን ጋር በእጅጉ የተላተመ ነው። የፖለቲካው ስብራት ያመጣው ትልቁ መጥፎ ጠባሳ የጋራ ትርክትን አዳክሞ የልዩነት፣ የመጠፋፋት እና የጥላቻ ትርክትን ማንገሡ ነው።

አንዱን አግልሎ እና ሙሉ ለሙሉ አሸንፎ ሥልጣን ላይ የመውጣት የዜሮ ድምር ፖለቲካ የኢትዮጵያ ትልቁ በሽታ ነው።

ይህ አካሄድ እርስ በርስ የመደጋገፍና ችግርን የመካፈል መልካም ባህላችንን በመሸርሸር፣ እኔ ካልመራሁ ሀገር ትፍረስ ወደሚል አደገኛና ራስ ወዳድነት የተሞላበት አስተሳሰብ አሸጋግሮናል።

ይህ የውስጥ መከፋፈልና ቀውስ ደግሞ ለውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትና ተፅዕኖ ሰፊ በር ከፍቷል።

ኢትዮጵያ በዚህ የታሪክ አዙሪት ውስጥ ስታልፍ ሥጣኔዋን ማስቀጠል ተስኗታል። በሕብረት ለነጻነት በጦር የተዋደቁት ልጆቿ ድህነትን ለማጥፋት ባለመተባበራቸው የተሟላ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ ተስኗት ኖራለች።

የሚያሳዝነው እውነታ ይህን የፖለቲካ ቋጠሮ ለመፍታት የሚያስችል ለዘመናት የኖረ ድንቅ ሀገር በቀል የሽምግልና እና የዕርቅ ባህል እያለን በበቂ ሁኔታ አለመጠቀማችን ነው።

ችግሮቻችንን ከማኅበረሰባዊ እሴቶቻችን፣ ከሃይማኖት አባቶች ተሰሚነት እንዲሁም እንደ ገዳ፣ የጆካ፣ አባጋር፣ መካባን ከመሳሰሉ ጠንካራ ማኅበረሰባዊ የፍትሕ እና የዕርቅ ሥርዓቶቻችን ማዕቀፍ ውጪ በሆነ መንገድ ለመፍታት መሞከራችን ከባድ ዋጋ አስከፍሎናል።

ከውጭ በገቡ ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለሞች ብቻ ለመጓዝ መሞከራችን እና ባህላዊ የዕርቅ ሥርዓቶቻችንን ከፖለቲካ መጠቀሚያነት ነጻ አድርገን አለማጎልበታችን ለዛሬው የውይይት ባህል መጥፋት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል።

ታዲያ አሁን ምን ማድረግ አለብን?

መፍትሔው ወደ አውዳችን መመለስ ነው። የውጭ ተፅዕኖን ለመቋቋም መጀመሪያ የራስን ቤት ማጽዳት እና ሕብረትን ማጠናከር የግድ ይላል።

ፖለቲከኞች እና የሐሳብ መሪዎች የመሸናነፍ ሳይሆን የመደማመጥ እንዲሁም ለሀገር ሰላም ሲሉ ግትር የሆነ አቋምን የማለዘብ ባህልን በተግባር ሊያሳዩ ይገባል።

በተለይም ወጣቱ ትውልድ በዲጂታሉ ዓለም ያለውን ስሜታዊነት ወደ ጎን በመተው ምክንያታዊ ውይይቶችን ሊያበረታታ ይገባል።

ሚዲያው፣ የትምህርት ሥርዓቱ፣ የኪነ-ጥበብ ዘርፉ ካለፉት ቁስሎች ይልቅ ወደ ፊት በሚያገናኙን የጋራ እሴቶች እና የወደፊት ዕጣ ፈንታችን ላይ ሊያተኩር ግድ ይላል።

በዚህ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሚና እጅግ የጎላ ነው።

ኮሚሽኑ የጠፋውን የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ለመመለስ የተዘረጋ ዘመናዊ የቤተሰብ መሶባችን ሊሆን ይገባዋል።

አሁን የተጀመሩት የምክክር ሂደቶች ሁሉን አሳታፊ፣ ከፖለቲካዊ ጨዋታ ነጻ የሆኑ እና እውነተኛ ማኅበረሰባዊ ስብራቶቻችንን የሚጠግኑ እንዲሆኑ የሚቻለው ሁሉ ተደርጓል። 

ሀገራዊ ምክክሩ ባህላዊ የዕርቅ እሴቶቻችንን ከዘመናዊ የመንግሥት ግንባታ ጋር አዋሕዶ የዘለቄታ ሰላም የምናመጣበት ታላቅ ዕድል ነው።

በጠረጴዛ ዙሪያ የማይፈታ የትኛውም የፖለቲካ ችግር በጦር ሜዳ ዘላቂ መፍትሔ እንደማያገኝ ታሪካችን ከበቂ በላይ አስተምሮናል። 

በመሆኑም ሁላችንም ወደኋላ ከጎተተን እኔ እበልጥ ክፉ ልማድ ወጥተን ለምክክሩ ስኬት የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል።

በለሚ ታደሰ