“ልፋት የተስፋ ምልክት ነው” እንደሚባለው የመደመር ትውልድ በዳተኝነት እና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ የሚቀመጥ ሳይሆን፣ የተሻለች ሀገርን ለመገንባት በጽኑ ተስፋ የሚተጋ ትውልድ ነው።
ይህ ትውልድ መደመር ዝም ብሎ ስሜታዊ መፈክር ሳይሆን፣ ሀገሩን ከፍ የማድረግን ታላቅ ዓላማ በውኑ ዓለም ለመተርጎም በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ልፋትን፣ ጽናትን እና ፍጹም ሀገራዊ መሰጠትን የዕለት ተዕለት መመሪያው ያደረገ ነው።
ይህ ትውልድ ያለፉ የታሪክ ጠባሳዎችን መልሶ መላልሶ በመቆፈር ዛሬንና ነገን ከማድማት ይልቅ፣ በፍቅርና በዕርቅ የሚጠግን የፈውስ ኃይል ሆኖ የተነሣ ነው።
“መደመር በደልን፣ የተሰበረ ልብን በፍቅር ያክማል፣ ይጠግናል እንጂ መልሶ መላልሶ በመቆፈር አያደማም” የሚለው እውነት የትውልዱ ዋና መመሪያ ነው።
ካለፈው ስህተት ተምሮ፣ የትናንት ቁስል በተለያዩ የሰዎች ትንኮሳና የፖለቲካ ሴራዎች እንዳያመረቅዝ የሚያደርግ የምክክር መፍትሔን በመታጠቅ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና አንድነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ይሠራል።
ለመደመርና በአንድነት ወደፊት ለመጓዝ በሁሉም ነገር ላይ መግባባት ግዴታ እንዳልሆነ የሚረዳው የመደመር ትውልድ፣ ልዩነትን እንደ ውበትና እንደ ጸጋ እንጂ እንደ መተላለቂያ ምክንያት አይቆጥረውም።
የመደመር መንግሥት መጽሐፍ እንደሚለው “የሩቅ ዘመናት ታሪክ በውስጣችን እየኖረ፣ ባልኖርነው ሕይወትና ባላጠፋነው ጥፋት” እየተናቆሩ ከአፈር ሳይነሡ ወደ አፈር የመመለስን አውዳሚ አዙሪት የመደመር ትውልድ በበሰለ አስተሳሰብ ይሰብራል።
የዘመናችን የፖለቲካ ንግድ “በትናንት ቆምሮ ዛሬንና ነገን መብላት” መሆኑን በመረዳት፣ ትናንትን ትቶ ልዩነትን የተሻገረ የጋራ ዓላማና የጋራ ጥቅምን ማስቀደምን ምርጫው ያደረገም ነው።
ይህ ትውልድ ማንነታችን እንዳይለያይ ሆኖ የተሰናሰለ፣ እንዳይነጣጠል ሆኖ የተገመደና የተዋሐደ መሆኑን ሙሉ በሙሉ የሚያምን የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አናጺ ነው።
እውነተኛ ብልጽግና የዜጎችን ደኅንነት በተግባር ማረጋገጥ መሆኑን በመረዳት፣ ለነገዋ ሀገር አስተማማኝ መሠረት ይጥላል። በዚህ ዓይነቱ የጋራ መረዳት፣ ፍቅርና ትጋት ምክንያት ነው ዛሬ ላይ “ኢትዮጵያ ከምናስበው በላይ እየተገነባች” ያለችው፤ ይህ የጥልቀትና የብልጽግና ጉዞ ደግሞ የመደመር ትውልድ ለታሪክና ለዓለም የሚያሳየው ሕያው ምስክርነት ነው።
በበረከት ሽመልስ