Search

"የትግራይ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ ዳግም አይሳሳትም፤ ከፌዴራል መንግሥት ጎን ይቆማል!" - አክቲቪስት መለስ ብስራት

ረቡዕ ሰኔ 10, 2018 121

የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ከዚህ ቀደም "በመከተ" ስም ይዞት የነበረውን አቋም ሙሉ በሙሉ በመቀየር፣ አሁን ላይ ያንን አካሄድ ጭራሽ እንደማይደግፈው ተገለጸ።

ይልቁንም ዳያስፖራው ከፌዴራል መንግሥት ጎን በጽናት እንደሚቆም እና ሀገር አፍራሽ ኃይልን በትግል እንደሚጋፈጠው፣ ታዋቂው አክቲቪስት እና የዳያስፖራ አባል መለስ ብስራት ከኢቲቪ ትግርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስታውቀዋል።

ዳያስፖራው ካለፈው ስህተቱ የተማረ በመሆኑ እና የህወሓት ቡድን የራሱን ሥልጣን ለማራዘም ሲል ዳግም የጀመረውን የጦርነት ነጋሪት እንደማይቀበለው አቶ መለስ ብስራት ተናግረዋል።

በዚህ ሰዓት የትግራይ ዳያስፖራ እና ወጣቶች ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ተላላኪ ኃይሎች ጋር ለመሰለፍ ምንም ዓይነት በቂ ምክንያት የለም ብለዋል።

የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ በመስጠት፣ የሀገርን ሉዓላዊነት በመጣስ እና ባለማክበር "በብሔራዊ ጥቅም" ስም ቀን እና ሌሊት የሚቅበዘበዘው የህወሓት ዘረኛ ቡድን መሆኑንም አቶ መለስ ገልጸዋል።

የትግራይ ሕዝብ ላለፉት 50 ዓመታት በህወሓት አንጃ አማካኝነት ሲደርስበት የመጣው ሰቆቃ በቅቶታል፤ አሁን የክልሉ ሕዝብ የሚፈልገው ሀገር በጀመረችው የለውጥ ጉዞ ውስጥ ባለቤት ሆኖ እንዲለወጥ እንጂ፣ መልሶ ጦርነት እና መከራ ውስጥ መግባት አይደለም ሲሉም ገልጸዋል።

በአብርሃ ካሳ