የዘመናት ታሪኳን በአኩሪ የነፃነት ተጋድሎ ያሸበረቀችው እና ለጥቁር ህዝቦች ሁሉ የኩራት ምልክት የሆነችው አፍሪካዊቷ እንቁ ኢትዮጵያ፣ ዛሬ ደግሞ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ ላይ እንደ አዲስ የማለዳ ኮከብ ደምቃ እየታየች ነው።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሀገራችን የተከተለችው መደመራዊና ፍፁማዊ ሀገራዊ ጥቅምን ያስቀደመ የውጭ ግንኙነት ዕሳቤ፣ ሀገሪቱን ከአስርት ዓመታት የጂኦስትራቴጂያዊ ኩስመና በማላቀቅ የዓለም ኃያላን ዓይን በፍቅርና በአድናቆት የሚያርፍባት አንከር አገር አድርጓታል።
ትናንት የውስጥ ፈተናዎቿንና በውጭ ኃይሎች የተደቀኑባትን ጫናዎች በፅናት ተቋቁማ፣ ዛሬ በዲፕሎማሲው መስክ የብልፅግና፣ የጥበብ እና የልዕልና ተምሳሌት ለመሆን በቅታለች።
አዲስ አበባ ዛሬ የዓለም የፖለቲካ የልብ ትርታ የምትደመጥባት፣ የምስራቅም ሆነ የምዕራብ ታላላቅ መሪዎች በክብር የሚመላለሱባት የዲፕሎማሲ ማዕከል ሆናለች።
ባለፉት ጊዜያት ብቻ፡-
ከአውሮፓ ኃያላን ጋር፡ ከፈረንሳይ እና ከጣሊያን መሪዎች ጋር ተደጋጋሚ የጉብኝት ልውውጦች በማድረግ ታሪካዊ ግንኙነቷን ወደ ላቀ ስትራቴጂካዊ አጋርነት አሸጋግራለች።
ከምስራቅና መካከለኛው ምስራቅ ጋር፡ ከህንድ፣ ከሩሲያ፣ ከቱርክዬ፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ከሳዑዲ አረቢያ እና ከብራዚል ጋር ያላትን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ትስስር በተጨባጭ ወደ አዲስ ምዕራፍ አሳድጋለች።
የተመራጭነት ማማ፡ ይህ ጥበብ የተሞላው አካሄድ አገራችን የዓለም መሪዎች መርጠው ኦፊሻላዊ ጉብኝት የሚያደርጉባት፣ ልምዷና ተሞክሮዋ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆንባት የተከበረችና የምትፈለግ አገር እንድትሆን አድርጓታል።
በኃያላን አገራት መካከል የሚኖረውን ዓለም አቀፋዊ ፉክክር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ፍላጎት እንዳይጎዳ በጥንቃቄ በማስተዳደር፣ ሚዛናዊና ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ያማከለ ዲፕሎማሲ ማራመድ መቻሏ ትልቅ የለውጡ ዘመን የብስለት ቋንቋ ነው።
የዲፕሎማሲዋ ፈርጥ እና የብሪክስ (BRICS) አባልነት
የዚህ ሁሉ ያላሰለሰ የዲፕሎማሲያዊ ተጋድሎ እና የላቀ ራዕይ ማሳረጊያ የሆነው ደግሞ ሀገራችን የዓለምን የኢኮኖሚና ፖለቲካ ሚዛን ከስሩ እየቀየረ ያለው ታላቁ የBRICS ስብስብ አባል መሆኗ ነው።
ከ40 በላይ አገራት የዚህ ኃያል ስብስብ አባል ለመሆን በጠየቁበትና ከፍተኛ ፉክክር በታየበት መድረክ፣ ኢትዮጵያ በልዩ ሁኔታ ተመራጭ መሆን መቻሏ የዲፕሎማሲ አቅሟን፣ ታሪካዊ ክብደቷን እና ተወዳዳሪነቷን በጉልህ አሳይቷል። በእርግጥም ብሪክስ እጁን ዘርግቶ ተቀበላት የዲፕሎማሲዋ ፈርጥ ኢትዮጵያ!
ይህ ታሪካዊ ስኬት ከረዥም ጊዜ ሀገራዊ ስትራቴጂካዊ ፍላጎቷ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ፣ የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ቀደምት መስራችነቷን የሚያጠናክር እና የውጭ ጫናዎችን ወደ ትብብር የለወጠ የብስለት ማሳያ ነው።
ከታኅሣሥ 2016 ዓ.ም ጀምሮ የBRICS ሙሉ አባል መሆኗ፣ አገራችን በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን የተደማጭነት አድማስ በማስፋት፣ የደቡብ-ደቡብ ትብብርን እንድታጠናክር እና ብሔራዊ ክብሯን ከፍ እንድታደርግ ሰፊ የወርቅ በር ከፍቶላታል።
በአጠቃላይ፣ ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ውስጥ ያሳካችው የዲፕሎማሲ ገድል በአጋጣሚ የተፈጠረ ሳይሆን፣ ርዕዮተ ዓለማዊ ተቸካይነትን በመተው፣ ትላንትን፣ ዛሬንና ነገን ባስተሳሰረ ተራማጅና መደመራዊ ዕይታ የተመራ ነው።
ሀገራችን ወዳጅን በማብዛት፣ ሉዓላዊ ክብሯን በማስጠበቅና አዳዲስ አጋርነቶችን በመፍጠር፣ ለቀጠናው ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ የዲፕሎማሲ ማማ ሆና ቀጥላለች።
ከትናንት ኩስመና ወጥታ፣ የታደሰ ጂኦስትራቴጂያዊ አቅሟን አውጃ፣ የዓለምን ትኩረት የሳበችው ይህች አፍሪካዊት እንቁ፣ የነገው ትውልድ በኩራት የሚተርከውን ታሪክ ዛሬ ላይ በተግባር እየጻፈች ትገኛለች።