Search

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ እንድታስተናግድ ተመረጠች

ሓሙስ ሰኔ 11, 2018 43

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ገቨርናንስ ማዕከል ዋና ዓመታዊ መድረክ የሆነውን ሁለተኛውን የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ (APPS 2026) እንድታስተናግድ ተመረጠች።

ጉባኤው እ.ኤ.አ. በኦክቶበር 2026 መገባደጃ ላይ በአዲስ አበባ “ለዕድገት መምራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአፍሪካ ኢኮኖሚ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ቀራፂዎች” በሚል መሪ ቃል ይካሄዳል።

May be an image of one or more people, dais and textይህ ጉባኤ የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት፣ ተቋማትን ለማጠናከር እና በአህጉሪቱ ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን ለማምጣት ያላቸውን ወሳኝ ሚና የሚያጎላ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ይህንን ታላቅ መድረክ እንድታስተናግድ መመረጧ የፖለቲካ ፓርቲ ተቋማትን በመጠቀም የዲሞክራሲ መታደስን፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያን እና ሀገራዊ ልማትን ለማፋጠን የምታደርገው ጥረት አህጉራዊ ዕውቅና እያገኘ መምጣቱን ያሳያል።

የመጀመሪያው የፓርቲዎች ጉባኤ እ.ኤ.አ. በኦገስት 2025 በጋና አክራ በከፍተኛ ስኬት መካሄዱና ልማት ተኮር ፖለቲካን ለማራመድ የጋራ ቁርጠኝነት የተንጸባረቀበትን የታሪካዊውን “የአክራ መግለጫ” (Accra Declaration) በማጽደቅ መጠናቀቁ ይታወሳል።

ለዚሁ የ2026ቱ አህጉራዊ ጉባኤ የሚደረገውን ዝግጅት አስመልክቶ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ዛሬ የአፍሪካ ገቨርናንስ ማዕከል የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ሰብሳቢ ቤኔዲክታ ላሲን በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይቱ ወቅት አቶ አደም ፋራህ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ገንቢ ውይይት እንዲኖር የሚያስችሉ እና ፓርቲዎች ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ለኢኮኖሚ ሽግግርና ለአህጉራዊ ልማት የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ የሚያጠናክሩ አፍሪካውያን እራሳቸው የሚመሯቸው መድረኮች መኖራቸው ያለውን ጠቀሜታ አጉልተዋል።

ሁለቱም ወገኖች የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ተሳትፎ ባለፈ የፖሊሲ ፈጠራ፣ የአመራር ልማት፣ የሀገር ግንባታ እና የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ መሪነት ሚናቸውን የሚወጡ ጠንካራ ተቋማት መሆን እንዳለባቸው አስምረውበታል።

በተጨማሪም የጉባኤውን ስኬት ለማረጋገጥ እና የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአህጉሪቱ ለሚመጣው ሁሉን አቀፍ ሽግግር ቁልፍ አንቀሳቃሽ ኃይል ለማድረግ በጋራ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

በዚህ ጉባኤ ላይ የሀገራት መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጭዎች፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እና ምሁራን የሚሳተፉ ሲሆን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር እንዴት የበለጠ ውጤታማ አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚችሉ በሰፊው ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።