Search

የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና እና የኦንላይን ዝግጅት

ሓሙስ ሰኔ 11, 2018 42

የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የደኅንነትና የቴክኒክ ቁጥጥር ሥራዎችን በማጠናከር፣ የፈተና ስርቆትና ኩረጃን በይበልጥ ለመከላከል የሚያስችሉ የውስጥ አሠራሮች መዘርጋታቸውን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ገለጹ።

ይህ ማሻሻያ ፈተናው ፍትሐዊና ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የሚያግዝ ሲሆን፣ ከሀገር ውጪ ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩ የዲጂታል ሲስተሞችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ የመተካትና አብዛኛውን ተማሪ በኦንላይን የመፈተን ሥራ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተከናወነ ይገኛል።

May be an image of one or more people, people studying, table and text

 

 

በዘንድሮው ፈተና ከተመዘገቡት 563 ሺህ 858 ተማሪዎች መካከል 306 ሺህ 707ቱ በተፈጥሮ ሳይንስ፣ 257 ሺህ 150 ያህሉ ደግሞ በማኅበራዊ ሳይንስ የሚፈተኑ ሲሆን፣ የመሠረተ ልማት ግንባታ ባልተጠናቀቀባቸው አካባቢዎች ቁጥሩ ከፍ ዝቅ ሊልና ወደ ወረቀት ፈተና ሊመለስ እንደሚችል ተጠቁሟል።

May be an image of studying and text

የሳይበር ጥቃቶችንና የበፈተና ወቅት የሚከሰትን ማጭበርበር ለመከላከል የሚያስችል ቴክኒካዊ ሲስተም የተዘጋጀ ሲሆን፣ የጸጥታ አካላትም የ24 ሰዓት ተቋማዊና አካላዊ ጥበቃ ያደርጋሉ ብለዋል።

በተጨማሪም ሊያጋጥሙ ለሚችሉ ያልተጠበቁ ችግሮች ሁሉ አስተማማኝ የአማራጭ ዕቅዶች (ባካፕ ፕላን) ተዘጋጅተዋል ነው ያሉት።

ተማሪዎች ከኮምፒውተር ስክሪን ጋር እንዲላመዱና የኪቦርድና ማውዝ አጠቃቀም ክፍተቶችን ለመቅረፍ ላለፈው አንድ ወር ተኩል የልምምድ ሥልጠና ሲሰጥ መቆየቱንና በሚጠበቀው ልክ ላልተለማመዱ ልጆች ደግሞ ከክልሎች ጋር በመናበብ የክትትልና ድጋፍ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለየት ያለ ድጋፍ ለሚሹና አካል ጉዳተኛ ለሆኑ ተፈታኞች፣ ለምሳሌ ለዐይነ ስውራን አንባቢ የመመደብ፣ ምቹ ክፍል የማዘጋጀትና ረዳት የማቆየት ዝግጅቶች ተጠናቀዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ የፈተና ስርቆትና ኩረጃ ወንጀልም ነውርም መሆኑን በመረዳት፣ የትምህርት አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ ተፈታኞችና ወላጆች ለዚህ ድርጊት እንዳይተባበሩና ጥፋት ፈጻሚዎችንም በሕግ እንዲጠይቁ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።