Search

ሚዲያዎች የማኅበረሰብ ትስስርን በማጉላት ለሀገራዊ አንድነት መጠናከር ሊሰሩ ይገባል፡- የሰላም ሚኒስቴር

ሓሙስ ሰኔ 11, 2018 38

የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ጋር በመቀናጀት "የሚዲያ ተቋማት ሚና ለሰላም ግንባታ" በሚል ርዕስ ያዘጋጁት የምክክር መድረክ በሐዋሳ ከተማ ተካሂዷል።

May be an image of newsroom and dais

በምክክር መድረኩ ላይ የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኬይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ ሚዲያ በአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ሂደት ላይ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ ጎኑ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተቋማቱ በኃላፊነት ስሜትና በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋሉ ለዘላቂ ሰላምና ለብሔራዊ መግባባት ያላቸው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ሚዲያዎች የማኅበረሰቡን የጋራ እሴቶች በማጉላት ለብሔራዊ ጥቅሞች ስኬት ዜጎች የጋራ አረዳድ እንዲኖራቸው ሊሠሩ እንደሚገባ የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በተለይም አሁን ባለንበት የድኅረ-እውነት ዘመን መገናኛ ብዙኃን ሕዝቡ ለዘመናት ጠብቆ ያኖራቸውን ማኅበረ-ባህላዊ ሀብቶች በማስተዋወቅና ሰላምን በማስረጽ ረገድ የማይተካ ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ሚዲያዎች የሕዝብን ወንድማማችነት፣ አንድነትና ሰላምን በመገንባት ቴክኖሎጂው የፈጠረውን የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት የማክሸፍ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸውና ከግጭት ጋር የተያያዙ ችግሮችን በዲጂታል ሥርዓት ለመፍታት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

 መገናኛ ብዙኃን የማኅበረሰቡ የምክክር ማዕከል ሆነው ለማገልገል ከፍተኛ ሚና ያላቸው በመሆኑ መንግሥት ከእነሱ ጋር ያለውን የጋራ ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፣ የሰላም ሚኒስቴር የብዙኃን መገናኛ ተቋማትን በማስተባበር ለሀገራዊ ሰላም እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በመድረኩ ላይ በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አወቀ አጥናፉ (ዶ/ር) "ሚዲያን የሚመሩ እና የሚያስተዳድሩ ሕጎች" በሚል ርዕስ የመወያያ ሰነድ አቅርበው ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፤ ከተለያዩ ክልሎች የመጡ የሚዲያ አመራሮች፣ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች፣ የቴሌቪዥንና የማኅበረሰብ ሬዲዮ ባለሙያዎች እንዲሁም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በጋራ ተሳትፈውበታል።