የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የመከላከያ ሳይበር ማዕከል ያሰለጠናቸውን መሠረታዊ የሳይበር ባለሙያዎች ባስመረቁበት ወቅት፣ ሀገራዊና ተቋማዊ ደህንነትን ከጥቃት ለመጠበቅ የሳይበር ዐውድ ዝግጁነትን ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ዋና አዛዡ፣ የሳይበር ጥቃት የሀገርን ሉዓላዊነት በከፍተኛ ደረጃ የሚፈታተን መሆኑን ጠቅሰው መከላከያ ሠራዊቱ በዚህ ምህዳር ያለውን ዝግጁነት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ሠራዊቱ ከለውጡ በፊት በአየር እና በምድር ኃይል ብቻ ተዋቅሮ እንደነበር ያስታወሱት ሌተናል ጄኔራል ይልማ፣ ከለውጡ ወዲህ የባህር ኃይል እና የሳይበር አደረጃጀቶችን በማካተት ዘመኑ ከደረሰበት የቴክኖሎጂ ምጥቀት ጋር ራሱን እያዋሃደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህ የለውጥ ጉዞም የሳይበር ምህዳርን አደረጃጀት በከፍተኛ ሁኔታ በማሻሻል፣ በሀገር ህልውና ላይ የሚቃጡ ውስጣዊና ውጫዊ ጥቃቶችን በብቃት ማክሸፍ መቻሉን አብራርተዋል።
በአሁኑ ጊዜ ዲጂታላዊ አሠራሮች በፍጥነት እየሰፉና እየተቀየሩ በመምጣታቸው የሳይበር ጥቃት የጦር ሜዳን የውጊያ አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ሊፈታተን እንደሚችል አመላክተዋል። በመሆኑም የሀገርን ሉዓላዊነትና ተቋማዊ ዲጂታል ሀብቶችን ሌት ተቀን ነቅቶ መጠበቅ ዘመኑ የሚጠይቀው አንገብጋቢ ተግባር መሆኑን አብራርተዋል።
እነዚህን ዘመናዊ የደህንነት ስጋቶች ለመቀልበስ ማዕከሉ የሠራዊቱን የሳይበር ላይ ንቃተ ህሊና የሚያሳድጉ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችንና መደበኛ ትምህርቶችን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
በመጨረሻም ማዕከሉ ወደፊት የሳይበር ኃይሉን በብዛትና በጥራት የማብቃት ተግባሩን ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ የጠቆሙት ዋና አዛዡ፣ ተመራቂ የሳይበር ሠራዊት አባላትም የገበዩትን እውቀት በከፍተኛ ወታደራዊ ዲስፕሊንና የኃላፊነት ስሜት በተቋማቸው በተግባር ላይ እንዲያውሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።