Search

ምክር ቤቱ የኦዲት ግድፈት በተገኘባቸው የመንግሥት ተቋማት ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ አሳሰበ

ሓሙስ ሰኔ 11, 2018 50

 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ 26ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።

ምክር ቤቱ በዋናነት ያደመጠው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የ2017 በጀት ዓመት የሒሳብ የፋይናንሺያል፣ የሕጋዊነት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርትን ነው።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት፤ በመሥሪያ ቤቱ በኩል በበጀት ዓመቱ 163 ተቋማትን ኦዲት በማድረግ የዕቅዱን 111 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት ከተመዘገቡት የኦዲት ግኝቶች ጋር ሲነጻጸር፣ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መሆኑን እና ለዚህም የመንግሥት ተቋማት የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ አሠራርን መተግበራቸው ለኦዲት ሥራውም ሆነ ለቁጥጥሩ ትልቅ አጋዥ መሆኑን አንስተዋል።

ሪፖርቱ አበረታች መሻሻሎችን ቢያሳይም፣ በገቢ አሰባሰብ እና በበጀት አጠቃቀም ረገድ ያሉ ክፍተቶች አሁንም አሳሳቢ ሆነው መቀጠላቸው ተጠቁሟል።

May be an image of one or more people and dais

ዋና ኦዲተሯ በመንግሥት የገቢ አሰባሰብ ሒደት ላይ ባለው ክፍተት ምክንያት 6.8 ቢሊዮን ብር ያልተሰበሰበ ቀረጥና ታክስ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ በቀጣይ ጥብቅ ክትትልና ጥረት መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

የአሠራር እና የመመሪያ ግድፈቶችም የሪፖርቱ ሌላው ማጠንጠኛ የነበሩ ሲሆን፣ በተለይም በከፍተኛ የመንግሥት የትምህርት ተቋማት ላይ አዋጅን መሠረት ያላደረገ የግዥ ሂደት እና የቆዩ የውዝፍ ዕዳዎች ችግር በስፋት መታየቱ ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም ሳይንቀሳቀስና ሥራ ላይ ሳይውል የተቀመጠ 6.9 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት በኦዲት ግኝቱ ላይ ተመላክቷል።

በየተቋማቱ የታዩ የኦዲት ግኝቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳዩ የመጡት በኦዲት ተደራጊና አድራጊ መሥሪያ ቤቶች የተቀናጀ አሠራር እንዲሁም በባለሙያዎች አቅም ግንባታ የተነሳ እንደሆነ ቢጠቀስም፣ ምክር ቤቱ በተገኙት ግድፈቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርግ ተጠይቋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በቀረበው የኦዲት ሪፖርት ላይ ሰፊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፤ የመንግሥት ሀብትና ንብረት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ግድፈት በተገኘባቸው ተቋማት ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እና ክትትል ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።