በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እጅግ አከራካሪ ከሆኑ ዘመናት አንዱ የልጅ ኢያሱ ዘመን መሆኑንና የመሪነታቸው፣ የመታሰራቸው እንዲሁም በመጨረሻም የሞታቸው ነገር ደብዝዞ እንዲያልፍ መደረጉን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገልጸዋል።
ልጅ ኢያሱ የሕዝብን እና የሃይማኖቶችን ትሥሥር ለመፍጠር በራሳቸው መንገድ ጥረት ማድረጋቸውን ያስታወሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አዳዲስ አሠራሮችንና ሕጎችን እንዳስተዋወቁ እንዲሁም ወደ ሕዝብ ቀረብ ያለ ሥርዓት ለመገንባት መሞከራቸውንም ገልጸዋል።
በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ጋራ ሙለታ የሚገኘው የልጅ ኢያሱ እሥር ቤት ብዙ ታሪካዊ ክስተቶችን የሚያስታውሰን ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ይህም የሀገራችን ፖለቲካ ከመቶ ዓመት በኋላም ቢሆን ከመበቃቀል መንገድ ለምን መውጣት አቃተው? ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል ብለዋል።
ይህ ታሪካዊ እውነታ ኢትዮጵያ “በፍቅር እንደመር፣ በይቅርታ እንሻገር” በማለት ያስቀመጠችውን መርህ አስፈላጊነት ይበልጥ የሚያስረዳ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መደመር እና ብሔራዊ ምክክር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ ያስተምረናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ምስራቅ ሐረርጌ ዞን አካባቢውን አመቻችቶ ከታሪካችን እንድንማር የሚያደርገው ጥረት በሁላችንም ሊደገፍ የሚገባ ነውሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።