የሰው ልጅ የሥልጣኔ ማማ፣ የዕድገትና የመሻገር ምስጢር በመነጋገር፣ በመደማመጥ እና የሀሳብ ልዕልናን በማክበር ላይ የተመሠረተ ነው። ነገር ግን፣ ዛሬ ላይ ቆመን ራሳችንን በሐቅ ልንጠይቅ ይገባል፤ እ... ምን ቀረን፣ ካለመመካከር ውጪ? ለምንስ ተመካክረን አንሞክረውም? ወይስ ደግመን እንታኮስ?
ባለፉት ዘመናት የሃሳብ ልዩነቶችን በአግባቡ ማስተናገድ አቅቶን አሰቃቂ ዋጋ ስንከፍል ኖረናል።
የሃሳብ ልዩነትን በአግባቡ ማስተናገድ አቅቶን ዜጎች ከሀገር ተሰደዋል፣ በሃሳብ ልዩነት ብዙ ወጣቶች ሞተዋል፣ አንድ ትውልድ ረግፏል። አንዱን ገሎ ስልጣን ላይ መውጣት፣ የተለየ ሀሳብን ማጥፋት እና ስልጣንን ከጠመንጃ አፈሙዝ ብቻ መፈለግ የፖለቲካችን ዋነኛ መገለጫ ሆኖ ቆይቷል።
ይህ ሰው ወለድ ጭቆና እና ጠባብ የፖለቲካ እይታ፣ ሀገሪቱን ጽንፍ የያዙ ነጠላ ትርክቶች እንድትታመስና ሀገራዊ የጋራ ትርክት እንዳይኖረን በማድረግ እጅግ ውድ ዋጋ አስከፍሎናል።
እስኪ ቆም ብለን ወደ ሌሎች እንመልከት፤ አውሮፓውያን በምክንያታዊነት ዘመን (Period of Enlightenment) በጠረጴዛ ዙሪያ ሃሳቦቻቸውን ሞግተው፣ የሰላ የሃሳብ ፍጭት አድርገው፣ ልዩነቶቻቸውን አቻችለው ጠንካራ ሀገረ መንግሥታትን መገንባት ችለዋል። የፓርላማና የሊበራል አመለካከቶችን በማዳበር በማይናጋ መሠረት ላይ የቆመ የፖለቲካ ማህበረሰብ ፈጥረዋል።
ታዲያ እኛ ምን ያንሰናል? አባቶቻችን በባህላዊ እሴቶቻቸው ተመካክረው ታላላቅ ሥልጣኔዎችን በገነቡበት ሀገር፣ ዛሬ እኛ ለመመካከር ምጥ የሚይዘን ለምንድን ነው?
ላለፉት ዘመናት ውይይትን የሚጸየፉ እና የተለየ ሀሳብን የሚጠሉ መንግሥታት በነበሩበት ሀገር፣ ዛሬ የመመካከርን በሮች ወለል አድርጎ የከፈተ እና "የሀገራችንን ቀሪ ዕጣ ፈንታ በጋራ እንወስን" የሚል የለውጥ መንግሥት እና ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር ተፈጥሯል።
ስለሆነም፣ ይህ ትውልድ ከፊቱ ሁለት ግልጽና ወሳኝ ምርጫዎች ቀርበውለታል፡-
• ወደ ሀሳብ ጠረጴዛ መምጣት፣ መወያየት፣ በመነጋገር ውስጥ የሀሳብ ልዩነቶችን ማጥበብ፣ የጋራ አቋም መያዝና ብሔራዊ መግባባት ፈጥሮ ሀገርን ማዳን። ይህ አካሄድ የተሰበረውን ሀገረ መንግሥት ለመጠገንና በህዝብ ዘንድ ቅቡልነት ያለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል ብቸኛው አማራጭ ነው።
• የጥፋት መንገድ፣ ውይይትን መግፋት፣ እንዳለፉት ጊዜያት እርስ በርስ መጠፋፋት፣ እየተታኮሱ መኖር እና የደም ዘመን እንዲቀጥል ማድረግ።
አሁን በተከፈተው የውይይት መድረክ ላይ አለመሳተፍ፣ ለመነጋገር ፈቃደኛ አለመሆን እና መመካከርን መጥላት አመፀኝነት ነው።
የሰላምን በር ዘግቶ የጥፋትን መንገድ መምረጥ የሀገርን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል ታሪካዊ ስህተት ነው። ያልተመካከረ ውግዝ ነው፤ ያልተመካከረ አመፀኛ ነው!
እኛ ኢትዮጵያውያን የትናንት ገናና ታሪክ፣ ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር፣ በመከራም በደስታም አብሮ የመቆም ልምድ እና የዳበሩ ባህላዊ የዴሞክራሲ እሴቶች ያሉን ህዝቦች ነን። እነዚህን ነባር እሴቶች ተጠቅመን፣ ሁሉንም ህዝቦች በእኩልነት የሚያስተናግድ አሳታፊና አካታች የሆነ የመግባባት ዴሞክራሲ ማነጽ ይጠበቅብናል።
በመሆኑም፣ ዛሬ ላይ ዴሞክራሲ፣ መወያየት እና ብሔራዊ ምክክር ለኢትዮጵያውያን የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን የሕልውና ጥያቄ ነው። ሀገራችንን ጥቂቶች ብቻቸውን ሮጠው ሊያሻግሯት አይችሉም፤ ኢትዮጵያ የምትገነባውና የምትጸናው በሁሉም ልጆቿ የነቃ ትብብርና ተሳትፎ ብቻ ነው።
እጣ ፈንታችን በእጃችን ነው፤ ከመመካከር ብዙ ነገር አለ፣ ካለመመካከር ምንም! የተከፈተልንን የመመካከር ዕድል ተጠቅመን ኢትዮጵያን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት በአንድነት እንነሳ!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ