ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ያስመዘገበችው ውጤት ከአካባቢ ጥበቃ የዘለለ ሰፊና ስትራቴጂያዊ ፋይዳ ያለው ነው።
ይህ ሀገራዊ ንቅናቄ የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባት፣ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶቿን በማጠናከር እና ለቀጣናዊ የአየር ንብረት መዛባት መፍትሄ በመስጠት ረገድ የማይተካ ሚና ተጫውቷል።
አረንጓዴ ዐሻራ ሀገራችን ለልማት እና ለአካባቢ ጥበቃ ባላት ቁርጠኝነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቅ ሀገር አድርጓታል።
የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ አረንጓዴ በማልበስ እና የደን ሽፋንን በማሳደግ የተገኘው ውጤት ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ፈተናዎች ያሏት በፈጠራ የታገዙ ምላሾች ማሳያ ነው።
አረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያን ለዘላቂ ልማት እንደምትሠራ የተፈጥሮ ሀብት ተንከባካቢ አርዓያ አድርጎ በማቅረብ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን ተቀባይነት ከፍ አድርጓል።
ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ የደን ልማት ሥራዎች ላይ በማሳተፍ በጋራ ሰላምና ጥቅም ላይ የተመሠረተ ቀጣናዊ ትስስርን አጠናክሯል።
በዚህም በአካባቢው ሀገራት መካከል የጋራ መተማመንን በመገንባት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ይበልጥ እንዲጠናከሩ አስችሏል።
አረንጓዴ ዐሻራ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በጋራ ከመትከል ባሻገር የተተከሉትን በመንከባከብ በዜጎች ዘንድ የባለቤትነት ስሜት እንዲዳብር አድርጓል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ የታገዘ የዲጂታል ልህቀትን ከአረንጓዴ ዐሻራ ጋር በማጣመር ለቀጣዩ ትውልድ የማይጠፋ የልማት ዐሻራ እያኖረች ነው።
በጥቅሉ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ በማፋጠን ላይ የሚገኘው የዚህ አረንጓዴ አብዮት ስኬት፣ ሕዝብ ለሀገሩ በአንድነት ሲቆም ምን ያህል ታላላቅ ሥራዎችን መከወን እንደሚችል ሕያው ምስክር ነው።
በሃና ምንዳሁን