(የዕለቱ መልዕክት)
የአንድ ጠንካራ ቤት ጽናት የሚለካው በተጋደሙት ማገሮቹ ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን፣ በቆሙት ምሰሶዎቹ እና በጣራው መስተጋብር ጭምር ነው።
“ድር እና ማግ ከተባበሩ ጨርቅ ይሆናሉ፤ አንዱ ካነሰ ግን ራቁትነትን አይሸፍንም” እንደሚባለው፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ይህንን እውነት በጉልህ ያሳስበናል።
ኢትዮጵያ ለዘመናት በአንድነት ስም ብዝኃነትን፣ በብዝኃነትም ስም አንድነትን የመሸርሸር አዙሪት ውስጥ ስትማስን ኖራለች።
አሁን ግን ይህንን የዜሮ ድምር ፖለቲካ ሰብሮ ለአንድነት ቦታ ከማይሰጥ ጽንፍ የወጣ ኅብረ ብሔራዊነት እና ለኅብረ ብሔራዊነት ቦታ ከማይሰጥ አምባገነናዊ አንድነት የወጣ፣ ሁለቱንም እሴቶች የያዘ ሚዛናዊ ውህደት ለመገንባት የተጀመረው ሥራ የሕልውና ጉዳይ ነው።
እውነተኛ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ማለት የአንድነት እና የብዝኃነት ውህደት ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም አንዱ የሌላውን ሕልውና የሚያጸናበት፣ ልዩነት እንደ መርገም ሳይሆን እንደ ጸጋ የሚታይበት ሥነ ሕይወታዊ ትሥሥር ነው።

ኢትዮጵያ የየራሳቸው ታሪክ እና ማንነት ያላቸው፣ ነገር ግን በባህል እና በደም እጅግ የተሣሠሩ ሕዝቦች ሀገር መሆኗ ሊታለፍ የማይችል እውነት ነው።
የመደመር መንግሥት ይህንን ቀመር በመረዳት ሁለቱን ጽንፎች ለማስታረቅ የያዘው አቅጣጫ ሊበረታታ የሚገባ ነው። ይህ እሳቤ ከፖለቲካ ዕቅድ ተሻግሮ ዜጎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሚያዩት እውነታ ሊሆን የሚችለው ግን፣ ገለልተኛ እና ጠንካራ ተቋማት ሲገነቡ ነው።
ትርክቶች ሲጋጩ ታሪክ ይቆስላል፤ የሚያቀራርቡ እውነታዎች ሲጎድሉ ደግሞ መፃኢው ትውልድ ተስፋ ይቆርጣል። አሮጌ ቁስልን ሁልጊዜ መጎርጎር ደም እንጂ ፈውስ አያመጣምና፣ ካለፉት ታሪካዊ በደሎች ቁርሾን ከመፈልፈል ይልቅ ስህተቶችን አርሞ ለወዳጅነት መጠናከር መሥራት የብልሆች ምርጫ ሊሆን ይገባል።
የሀገረ መንግሥት ግንባታ ረጅም እና እልህ አስጨራሽ ጉዞ ነው። በኢኮኖሚው ረገድ የሚታዩት የግብርና ስኬቶች እና ግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ እንዲሁም በቱሪዝም እና በንግድ መስኮች የተዘረጉት አማራጮች የሀገርን የጀርባ አጥንት የሚያጠነክሩ መሆናቸው አይካድም።
እውነተኛው ሀገራዊ ከፍታ የሚለካው በዜጎች እኩልነት፣ በፍትሕ እና በሲቪል ሰርቪስ ተቋማቱ ገለልተኝነት እና ታማኝነት ላይ ነው።
መንግሥት በእነዚህ ተቋማት ላይ የጀመራቸው የሪፎርም ሥራዎች በተስፋ ሰጪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ሒደቱ የሕዝብን ሙሉ አመኔታ ያተረፈ እንዲሆን የማያቋርጥ የዜጎች ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ነው። ተቋማዊ ነጻነታቸው ከግለሰቦች እና ከፓርቲ ፍላጎት በላይ ሊጠበቅ እና ሊከበር ይገባል።
ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷ ተከብሮ የቆየው በሕዝቦቿ የጋራ አርበኝነትና ደም ነው። ዛሬ የምንገነባው የብዝኃ ቋንቋ ፖሊሲና አካታች ሥርዓት፣ ያንን ታሪካዊ አርበኝነት ወደ ዘመናዊ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ግንባታ የማሸጋገሪያ ድልድይ ሊሆን ይገባል።
“በኅብረት ሆነን እንበለጽጋለን፤ በልጽገንም በኅብረት እንኖራለን” የሚለው መርህ ከፖለቲካ ፍጆታ ባለፈ እውን ሊሆን የሚችለው፣ የሁሉም ኢትዮጵያውያንና የብሔሮች መብት መከበር ተግባራዊ ሲሆን ነው።
ሀገር የምትጸናው በተቋማት ልዕልና በመሆኑ፣ ብዝኃነትን በአግባቡ ማስተናገድ የሚችል እውነተኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት መገንባት የነገዋን ብሩህ ኢትዮጵያ ማረጋገጫ ብቸኛው መንገድ ነው።
ሁላችንም ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር እና ለጋራ ብልጽግና በአንድነት የምንቆምበት ጊዜው አሁን ነው።
የኢቢሲ ዶትስትሪም ኤዲቶሪያል