Search

ውቢቷ አርባ ምንጭ የቱሪዝምና የኢኮኖሚ ሽግግር ማዕከል

ዓርብ ሰኔ 26, 2018 38

የጋሞ ምድር እና ውቢቷ አርባ ምንጭ ከተማ ተፈጥሮን፣ ባህልን እና ዘመናዊ ልማትን በአንድነት ያዋሃዱ የሀገራችን ልዩ ተስፋዎች ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በተደጋጋሚ በአካባቢው ባደረጉት ጉብኝት እንዳረጋገጡት፣ ይህንን ምድረ ገነት በማኅበረሰቡ ትጋት እና በተቀናጀ የልማት ሥራ በማገዝ ትልቅ ምጣኔ-ሀብታዊ መስህብ ማድረግ ይቻላል።

የአካባቢው ማኅበረሰብ ለልማት ያለው ቁርጠኝነት ከመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ጋር ተደምሮ አርባ ምንጭን የኢኮኖሚ ሽግግር እና የቱሪዝም ማዕከል እያደረጓት ይገኛል።

ማራኪው የተፈጥሮ እና የባህል መስህብ

አርባ ምንጭ ስሟን ያገኘችው ከከተማዋ ግርጌ ከሚፈልቁት ማራኪ አርባ የተፈጥሮ ምንጮች ነው፡፡

ከተማዋን በቅርበት የሚያዋስኗትን የአባያ እና የጫሞ ሀይቆችን አስደናቂው "የእግዜር ድልድይ" ያስተሳስራቸዋል።

ከዚህም ባሻገር የስዋይንስ ቆላ አጋዘን እና የሜዳ አህያ የሚገኙበት የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ፣ እንዲሁም በጫሞ ሀይቅ የሚገኘው "የአዞ ገበያ" ግንባር ቀደም የቱሪስት መስህቦቿ ናቸው።

በደጋማው የጋሞ ክፍል የሚኖረው የዶርዜ ሕዝብ በበኩሉ በሽመና ጥበቡ፣ ባለ ሁለት ፎቅ በሚመስለው የቀርከሃ ጎጆ አሠራሩ እና ከእንሰት በሚያዘጋጀው የምግብ ባህሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ የባህል ቱሪዝም ድምቀት ነው።

ግዙፉ የአርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው "ገበታ ለትውልድ" መርሐ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተመረጡ የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል የአርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርትን አካትቷል።

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በተለይ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን፣ ጉባኤዎችን እና ኤግዚቢሽኖችን በከፍተኛ ደረጃ ለማስተናገድ የተገነባ ነው።

ሪዞርቱ ዘመናዊ የእንግዳ ማረፊያ ክፍሎች እና ሰፋፊ የስብሰባ አዳራሾች አሉት፡፡ በሐይቁ ውኃ ላይ ተንሳፍፎ እየተሽከረከረ አገልግሎት የሚሰጠው ሬስቶራንት ልዩ የሥነ-ህንጻ ጥበብ መገለጫው ነው።

ሪዞርቱ የተፈጥሮ እና የባህል መስህቦችን በማስተሳሰር የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ከፍራፍሬ ቅርጫትነት እስከ ዘመናዊ የሀማሳ ሞዴል መንደር

በግብርናው ዘርፍ "የኢትዮጵያ የፍራፍሬ ቅርጫት" በመባል በሰፊው የሚታወቀው የአርባ ምንጭ አካባቢ፣ በኩታ ገጠም እርሻ ልማት እና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን በሚያሳድገው "ሌማት ትሩፋት" መርሐ ግብር ምርታማነቱን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል።

ይህንን ተከትሎ የገጠር ኮሪደር ልማት አካል የሆነው እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በይፋ የተመረቀው "የሀማሳ ሞዴል መንደር" የሪፎርሙ ህያው ፍሬ ሆኖ ብቅ ብሏል።

79.4 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ዘመናዊ መንደር የአርሶ አደሩን ኑሮ እና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያግዙ ዘመናዊ የመታጠቢያ ክፍሎችን፣ የእንስሳት ማደሪያን፣ የአትክልት ስፍራን፣ የባዮ ጋዝ እና የንብ ቀፎዎችን አሟልቶ በመያዝ ለነዋሪዎች ሁለንተናዊ ብልጽግናን እያረጋገጠ ይገኛል።

ይህ የልማት ሥራ የገጠሩን ማኅበረሰብ ክብር፣ ምቾት እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው።

በሙዝ እና ማንጎ ዛፎች ያጌጠው የኩልፎ ወንዝ ዳርቻ የኮሪደር ልማትም አካባቢውን ለእግረኞች እና ለብስክሌት እጅግ ምቹ አድርጎታል።

የሰላም እሴት ለዘላቂ ልማት

የጋሞ ምድር እና የአርባ ምንጭ ከተማ ያላቸውን እምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ ሀብትነት በመቀየር ረገድ የተጀመሩት ሥራዎች እጅግ ተስፋ ሰጪ ናቸው።

ማኅበረሰቡ ዘንድ ያሉትን እንደ "ደሬ ወጋ" እና "ዱቡሻ" የመሳሰሉ ባህላዊ የፍትህ እና የሰላም እሴቶችን ለሀገራዊ አንድነት በስፋት በመጠቀም፣ አካባቢው በሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የጎላ ሚና እንዲጫወት ማድረግ ያስፈልጋል።

ዘመናዊውን ኮንፈረንስ ሪዞርት ከተፈጥሮ እና ባህላዊ ፓርኮች ጋር በማስተሳሰር፣ እንዲሁም የፍራፍሬ ልማትን በማስፋፋት አካባቢውን የደቡብ ኢትዮጵያ ዋነኛ የአግሮ-ኢንዱስትሪ እና የቱሪዝም ማዕከል ማድረግ ተችሏል።

በለሚ ታደሰ