Search

ከበቀል ይልቅ ይቅርታ፡ ኢትዮጵያ ከጋሞ የሰላም እሴቶች ምን ታተርፋለች?

ዓርብ ሰኔ 26, 2018 47

ሁሉም የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ለዘመናት ያካበታቸው፣ በተግባር የተፈተኑ እና አብሮነትን ያጸኑ የሀገር በቀል የሰላም እና የዕርቅ ባህሎች አሉት።

እነዚህን ዕሴቶች ከተገኙበት ማኅበረሰብ አልፎ የጋራ የሀገር ሀብት ማድረግ ከቻልን ዛሬ ለገጠሙን ማኅበራዊ ፈተናዎች ትልቅ መፍትሔ ይሆናሉ።

ከእነዚህ ሕያው ዕሴቶች መካከል የጋሞ ማኅበረሰብ የዳበረ የማኅበራዊ ፍትሕ፣ የዕርቅ እና የጥበብ ፍልስፍና አንዱ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በተለያዩ መድረኮች ስለ ጋሞ ሕዝብ የሰላም ወዳድነት እና እርጋታ መስክረዋል፡፡ ማኅበረሰቡን እንደ ሀገር በቀል የሰላም ተምሳሌት አድርገው አጉልተውታል።

ለዚህም 2011 . በቡራዩ ከተማ እና አካባቢው የተከሰተውን አሳዛኝ ግጭት ተከትሎ የታየው ክስተት ዓይነተኛ ማሳያ ነው።

በወቅቱ የተፈጸመውን ጥቃት ሰምቶ ለበቀል የተነሳሳውን ወጣት፣ የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች በአርባ ምንጭ እና አካባቢው በእጃቸው እርጥብ ሳር በመያዝ እና በመንበርከክ ከጥፋት መመለሳቸው ዓለምን ያስደመመ የሰላም ፍልስፍና ተግባራዊ ማሳያ ነበር።

ይህ የሀገር ሽማግሌዎች ጥረት ሀገራችንን ከከፋ አደጋ በመታደግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ ታሪካዊ ክስተት ነው።

"ደሬ ወጋ" እና "ዱቡሻ" የፍትሕ ተቋማዊነት

የጋሞዎች ጥልቅ የሰላም ፍልስፍና የሚመነጨው "ደሬ ወጋ" ከተሰኘው ትውልድ ተሻጋሪ የፍትሕ እና የሕግ ሥርዓት ነው።

ማኅበረሰቡ የኑሮ ዘይቤውን፣ የንብረት ባለቤትነትን እና የአካባቢ ጥበቃን ጨምሮ አጠቃላይ ማኅበራዊ መስተጋብሩን የሚመራው በዚህ ሥርዓት ነው።

"ደሬ ወጋ" በተግባር የሚተረጎምበት "ዱቡሻ" የተሰኘው ባህላዊ አደባባይ ደግሞ ፍጹም እውነት ብቻ የሚነገርበት እና የፈጣሪ መንፈስ የሚገኝበት የተቀደሰ ስፍራ ተደርጎ ይታመናል።

ይህ የፍትሕ አደባባይ መንፈሳዊ ስፍራ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ማኅበራዊ ተቋምም መሆኑን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሶሲዮሎጂ እና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና ተመራማሪ የሆኑት ባይሳ ፌዬ (/) ለኢቢሲ ዶትስትሪም ተናግረዋል፡፡

እንደ / ባይሳ ማብራሪያ ዱቡሻ እንደ ስፍራ በጣም የተከበረ፣ እውነት እና ሃቅ ብቻ የሚነገርበት እንዲሁም ፍትሕ የመጨረሻዋን ባለቤት የምታገኝበት ተቋም ነው።

ተመራማሪው አክለውም፣ የዱቡሻ ተቋማዊ አደረጃጀት ከቤተሰብ እስከ ማኅበረሰብ የራሱ የሆነ እርከን እንዳለው ያስገነዝባሉ።

በታችኛው ዱቡሻ ያልተፈታ ጉዳይ ወደ ቀጣዩ እርከን እየተላለፈ፣ በሂደት የግለሰብም ሆነ የማኅበረሰብ ፍትህ ያለምንም መጓደል እንዲሰፍን ያደርጋል።

በዱቡሻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የሚቀርቡ ተከራካሪዎች ለወደፊት ትውልዳቸው ሲሉ እውነትን ብቻ እንዲናገሩ የሚደረገው ጥብቅ ማሳሰቢያ፣ ማኅበረሰቡ ለእውነት ያለውን የላቀ ክብር ማሳያ ነው ይላሉ / ባይሳ።

ሥነ-ልቦናዊ መሠረት እና የዕርቅ ሥርዓቱ

የጋሞ ባህላዊ ዳኝነት "ደሬ ጪማ" በሚባሉ ታማኝ፣ ገለልተኛ እና ስሜታቸውን መቆጣጠር በሚችሉ የሀገር ሽማግሌዎች የሚመራ ነው።

የሽምግልናው ዋና ዓላማ በዳይን መቅጣት ሳይሆን ማኅበራዊ መስተጋብርን መጠገን እና የተናጋውን ሰላም መመለስ ነው።

ማኅበረሰቡ ሕግን እንዲያከብር የሚያደርገው ትልቁ ሥነ-ልቦናዊ መሠረት "ጎሜ" የተሰኘው እምነት ነው።

ማኅበራዊ ደንብን መጣስ፣ መዋሸት ወይም አካባቢን መበከል በግለሰቡም ሆነ በሀገር ላይ መቅሰፍትን ያመጣል ተብሎ ስለሚታመን በዳይ በገዛ ፈቃዱ ጥፋቱን አምኖ ይቅርታ ይጠይቃል።

ግጭቶች ሲፈጠሩም "ቱጌ" በመሳሰሉ የዕርቅ ሥርዓቶች ታጅቦ ተበዳይ እና በዳይ "ማታ ኦፑት" የተባለውን ባህላዊ መጠጥ በጋራ በመጠጣት ፍጹም ዕርቅ ይፈጽማሉ።

የምሁራን ዕይታ እና ዓለም አቀፍ ዕውቅና

እነዚህ የጋሞ ማኅበረሰብ የሰላም እና የፍትሕ እሴቶች መሠረታዊ የሶሲዮሎጂ እውነታዎች መሆናቸው በልዩ ልዩ ምሁራዊ ጥናቶች ተረጋግጧል።

የአዲስ አበባ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች እነዚህን እሴቶች በማጥናት እና በማሳወቅ ረገድ ሰፊ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

በተለይም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ "ደሬ ወጋ" እና "ዱቡሻ" የዕርቅ ሥርዓቶችን በምርምር በማገዝ ወደ ሥርዓተ ትምህርት በማስገባት እና የባህል ማዕከላትን በመክፈት ሀገራዊ ፋይዳቸው የጎላ እንዲሆን የላቀ ሥራ እየሠራ ነው።

/ ባይሳ እንደገለጹት፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የጋሞን ባህላዊ የፍትሕ ማስፈን ሥርዓት ለዓለም በማሳወቅ ደረጃ በዚህ ዓመት 5 አህጉራት የተውጣጡ 17 ዓለም አቀፍ ምሁራንን ያሳተፈ የመስክ ትምህርት ተካዷል።

በአንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል አዘጋጅነት 5 ቀናት ምሁራኑ ማኅበረሰቡ መሀል ተቀምጠው ሥርዓቱን በቀጥታ ተምረው እንዲሄዱ መደረጉ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ተመራማሪው ጠቅሰዋል።

የጋሞ ሕዝብ የዕርቅ እና የሰላም ባህል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው።

እንደ ማኅበረሰብ እነዚህን በተግባር የተፈተኑ እሴቶች ከማድነቅ ባለፈ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የጋራ ልምምድ ልናደርጋቸው ይገባል።

ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት፣ እውነትን የመናገር እና ይቅር ለፈጣሪ የመባባል ባህሎቻችንን ካጎለበትን፣ ጠንካራ እና ሰላሟ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን መገንባት እንደምንችል የጋሞ ማኅበረሰብ ሕያው ምስክር ነው።

በለሚ ታደሰ