በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 የትምህርት ዘመን የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ማለፊያ ውጤት 50 በመቶ እንዲሆን ተወስኗል።
የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ አጠቃላይ ካውንስል አባላት ባካሄዱት መርሃ ግብር፣ የቀረበውን የማለፊያ ነጥብ በሙሉ ድምጽ አጽድቀዋል።
በዚህም መሰረት መደበኛ ተማሪዎች 50 በመቶ፣ አካል ጉዳተኞች 45 በመቶ እንዲሁም የኦቲስቲክ፣ ዳውን ሲንድረምና ኢንተሌክቹዋል ዲሴቢሊቲ ያለባቸው ተማሪዎች 40 በመቶ የማለፊያ ነጥብ እንዲሆን ተወስኗል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር)፤ ቢሮው በ2018 የትምህርት ዘመን የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የተለያዩ ተግባራት ማከናወኑን ገልጸዋል።
የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የማጠናከሪያ ትምህርት ከመሰጠቱ ባሻገር፣ በተለይም በሒሳብ እና በእንግሊዘኛ ትምህርቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ መደረጉ ለተመዘገበው ውጤት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ጠቁመዋል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሳምሶን መለሰ በበኩላቸው፤ በከተማ አስተዳደሩ በ2018 ዓ.ም 84 ሺህ 737 ተማሪዎች በ199 የፈተና ጣቢያዎች ፈተናውን መውሰዳቸውን ገልጸው፣ የዘንድሮው ውጤት ከዚህ ቀደም ከነበሩት ዓመታት አንጻር እድገት ማሳየቱን አስታውቀዋል።
ኃላፊዎቹ ፈተናውን በአጭር ጊዜ በማረም ውጤቱ ይፋ እንዲሆን ቀን ከሌት ለሰሩ የፈተና ክፍል ባለሙያዎች፣ ሂደቱን ለደገፉ አመራሮችና ለተመዘገበው ውጤት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: