Search

ለነገ ምጥቀት ዛሬ መሠረት እያኖረ ያለው የመደመር ዕሳቤ

ቅዳሜ መስከረም 09, 2019 72

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) "መደመር መንገድ" መጽሐፋቸው "በፈጣን ዓለም ውስጥ ቆሞ ማደግ የሚችለው ዛፍ እንጂ ሰው አይደለም" ሲሉ ያስቀመጡት እሳቤ 21ኛው ክፍለ ዘመንን የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ምኅዳር የሚመራ ጽኑ እውነት ነው።

ዛፍ በአንድ ስፍራ ተተክሎ እና ሥሩን ሰድዶ ያድጋል፤ ፈጣኑ የዓለማችን እውነታ ግን በአንድ ቦታ ረግቶ መቆምን በፍጹም አይፈቅድም።

በቋሚነት በሚለዋወጠው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ፣ የዲፕሎማሲ እና የኢኮኖሚ ውድድር ውስጥ ቆሞ ማደግ አይቻልም።

ረግቶ መቆም ወደኋላ መቅረትን አልፎም መሸነፍን መቀበል ነው። ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያረጋገጠችው ታላቅ እውነታም ይህንኑ የፍጥነት ፍልስፍና በተግባር የመተርጎም አቅሟን ነው።

የመደመር እሳቤ የተመዘገቡ ስኬቶችን እንደ ተተከለ ዛፍ ቆመው የሚቀሩ ሳይሆን፣ አዳዲስ የዕድገት አድማሶችን ለመክፈት የሚያገለግሉ የጉዞ ማስፈንጠሪያዎች አድርጎ ይመለከታቸዋል።

የዚህ ተለዋዋጭ እና ፈጣን ጉዞ የመጀመሪያው ማሳያ በዲጂታል ምኅዳሩ የታየው ንቅናቄ ነው። "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ የዛሬን ቴክኖሎጂያዊ ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ ለመፃኢው ጊዜ ጠንካራ መሠረት እየጣለ ይገኛል።

ወጣቶችን ኢንዱስትሪ 5.0’ አብዮት የሚያዘጋጀው "5 ሚሊዮን ኮደርስ" ኢኒሼቲቭ፣ 50 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ውስጥ ማቀፉ እንዲሁም የመንግሥት አገልግሎቶች ወደ ኤሌክትሮኒክ ሥርዓት መግባታቸው የዚሁ የፍጥነት ማረጋገጫዎች ናቸው።

የቴሌኮም ደንበኞች አጠቃላይ ቁጥር እና የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ምጣኔ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ማደጉ ኢትዮጵያ የዓለምን የቴክኖሎጂ ፍጥነት ለመቀላቀል ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ተወዳዳሪ ለመሆን የያዘችውን ጠንካራ ፍጥነት ያሳያል። እነዚህ ስኬቶች የተጠናቀቁ ግቦች ሳይሆኑ፣ የነገው የዲጂታል ኢኮኖሚ እግሮች ናቸው።

ይህ የተፋጠነ ምጥቀት በኃይል እና በኢነርጂ ዘርፍም የኢትዮጵያን አዲስ ገጽታ አጉልቶ አሳይቷል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የተበታተነ የሕዝብ አቅም ሲደመር የሚፈጥረውን ተዓምር አረጋግጧል።

ይህ ግድብ የውኃ ማጠራቀሚያ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ሽግግር የሚያፋጥን፣ ለጎረቤት ሀገራት አስተማማኝ የኃይል ምንጭ በመሆን ቀጣናዊ ትሥሥርን የሚያጠናክር እና ዘወትር የሚንቀሳቀስ ሕያው የልማት ሞተር ነው።

በግብርናው ዘርፍ የታየው ሥር ነቀል አሠራር የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጉዞን ከተለምዷዊው አዝጋሚ እርምጃ ያላቀቀ ነው።

በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እና በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተገኙ ስኬቶች፤ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች የሚካሄዱት የኮሪደር ልማቶች የተመዘገቡት ዐበይት ስኬቶች ኢትዮጵያ እንደ ዛፍ በአንድ ቦታ ተተክላ የምትቀር ሳትሆን፣ ከዘመኑ የፍጥነት ምኅዳር ጋር እኩል የምትራመድ መሆኗን በተግባር ያረጋገጡ ናቸው።

የተሠሩት ሥራዎች የትናንት ታሪኮች ወይም የስኬት ማጠቃለያዎች አይደሉም፤ ይልቁንም ሀገራችን በነገው ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የላቀ ተፅዕኖ ፈጣሪ እንድትሆን የተዘጋጁ፣ ቆሞ ካለመቅረት ፍልስፍና የሚመነጩ እና ወደ ተፋጠነ የምጥቀት ከፍታ የሚያመጥቁ ጽኑ የጉዞ ማስፈንጠሪያዎች ናቸው።

በለሚ ታደሰ

#Ethiopia #Medemer #DigitalEthiopia #GERD #GreenLegacy #EBC

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: