ቀያይ ሰይጣኖቹ በሜዳቸው በኦልድ ትራፎርድ ከተቀናቃኛቸው ማንችስተር ሲቲ ጋር ባደረጉት ጨዋታ የ 1 ለ 0 ሽንፈት ካስተናገዱ ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ በካራባኦ ካፕ ብራይተንን አስተናግደው 2 ለ 0 እየመሩ በስተመጨረሻ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ከውድድሩ ውጪ ሆነዋል።
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በተደረጉ የመጀመሪያ አራት ጨዋታዎች አራት ነጥብ ብቻ የሰበሰቡት ማንችስተር ዩናይትዶች፣ ወደ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች እረፍት ከማምራታቸው በፊት እሁድ ዕለት ከፉልሃም ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ድል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ማንችስተር ዩናይትድ ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች ያስመዘገበውን ደካማ ውጤት ተከትሎም በቡድኑ እና በአሰልጣኙ ላይ ከፍተኛ ትችቶች መሰማት ጀምረዋል፡፡
የቡድኑ አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ ግን ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ የሚሰጡ አስተያየቶች ሚዛናዊነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግሯል።
አሰልጣኙ ቡድኑ ከፉልሃም ጋር ከሚያደርገው ጨዋታ በፊት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ፤ የማንችስተር ዩናይትድ የሰሞነኛ የውጤት ማጣት ጉዞ አስደንጋጭ አልያም የዓለም መጨረሻም አይደለም ሲል ገልጿል።
ቡድኑ በጣም ረጅም በሆነና ከባድ በሚባል የሽንፈት ጉዞ ውስጥ አይደለም ያለው ማይክል ካሪክ፤ በቅርቡ ሁለት ጨዋታዎችን ተሸንፈናል፤ ነገር ግን በሁሉም ጨዋታዎች ላይ በጥሩ ተፎካካሪነት መጀመር ችለናል ሲል ተናግሯል።
በክለቡ እስካሁን ባለው ቆይታ ኩራት እንደሚሰማው የገለጸው አሰልጣኙ፣ አስቸጋሪ ጊዜያት ቡድኑን ይበልጥ ጠንካራ እንደሚያደርጉት ጠቅሷል።
አሰልጣኙ አክሎም፤ እራሳችንን በጥሩ የጨዋታ አቋም ላይ ለማስቀመጥ በርካታ መልካም ነገሮችን ሰርተናል፤ ስለዚህ እምነታችን የሚመጣው ከዚያ ነው፣ የሰራናቸው መልካም ነገሮች በዙሪያው ባለው አጠቃላይ ስሜት ምክንያት ሙሉ በሙሉ ይረሳሉ፣ እኛ ግን አንረሳውም ሲል ተናግሯል፡፡
ማይክል ካሪክ በሁለት ወይም በሶስት መጥፎ ውጤቶች ብቻ ስለወደፊቱ ጊዜ መጨነቅ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው ሲልም፤ በስራው ላይ ምንም ዓይነት ስጋት እንደሌለበት ገልጿል።
ካሪክ ባለፈው የውድድር ዘመን ከመራቸው 17 ጨዋታዎች ውስጥ 12ቱን ማሸነፍ ችሎ ነበር። ሆኖም አሁን ላይ ካደረጋቸው 6 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው ሁለቱን ብቻ በመሆኑ ከፍተኛ ትችት አስከትሎበታል።
ማንችስተር ዩናይትድ ረቡዕ ዕለት በብራይተን የደረሰበት ሽንፈት ደግሞ በክለቡ ታሪክ እ.ኤ.አ ከ1976 በኋላ በሜዳው 2 ለ 0 እየመራ ሲሸነፍ የመጀመሪያው ሆኖ ተመዝግቧል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: